በተያዘው በጀት ዓመት ግዢ እንዲፈጸምላቸው ላመለከቱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችና የፌዴራል ተቋማት ከ9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት ለማቅረብ ጨረታውን ላሸነፉ ድርጅቶች የአሸናፊነት ደብዳቤ መሰጠቱን ያስታወቀው የመንግሥት ግዥ አገልግሎት ነው።
ተቋሙ ግዢውን የሚፈጽመው በ5 ዋና ዋና የንብረት መደቦች ማለትም በጽሕፈት መሣሪያዎች፣ በኮምፒውተር ቀለም ወይም ቶነሮች፣ በአይ.ሲ.ቲ መገልገያዎች፣ በጽዳት ዕቃዎችና በደንብ ልብሶች ላይ መሆኑ ታውቋል።
የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ጎጃም ታደለ እንደገለጹት፣ ከተጠቃሚ መሥሪያ ቤቶች የተሟላ የመረጃ ፍላጎት ከተቀበሉ በኋላ የጨረታ ሂደት ተከናውኖ አሁን ላይ ለአቅራቢ ድርጅቶቹ የአሸናፊነት ደብዳቤ ተሰጥቷል።
በሌላ በኩል ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የ90 መሥሪያ ቤቶችን 271 ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችና ልዩ ልዩ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ 322 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመንግሥት ማስገኘቱን ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ለ178 የፌዴራል ተቋማት ግዢዎችን የመፈጸምና ያገለገሉ ንብረቶችን የማስወገድ ሥራዎችን የሚያከናውነው የመንግሥት ግዥ አገልግሎት፣ የዕቃዎች አቅርቦት ሂደቱ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል።
አሐዱ ሬዲዮ
