የአገርን የምግብ ሉዓላዊነትና ዋስትና ለማስጠበቅ በስራ ላይ የሚገኘው የመሬት አስተዳደር አዋጅ ተስተካክሎ አስተማማኝ ሰላም ሊሰፍን እንደሚገባ የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ተወካይ አቶ የሺዋስ አሰፋ ገለጹ።
የ4 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው የትብብሩ ተወካይ አቶ የሺዋስ ይህንን ያሉት አሐዱ ራድዮ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ሕብረት ጥምረት ጋር ባዘጋጀው የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ ነው፡፡
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የማንኛውም መንግሥት ቀዳሚ ግዴታ እና የዜጎች የሕልውና ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ተወካዩ፥ የምግብ ሉዓላዊነቱን ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ለአገር ውስጥና ለውጭ ተጽዕኖዎች በቀላሉ ተጋላጭ እንደሚሆን አብራርተዋል።
አቶ የሺዋስ አያይዘውም፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች በምርትና ምርታማነት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን፤ ግጭቶቹ አምራቹ ገበሬ በሰላም ውሎ እንዳያመርትና በተለያዩ የጸጥታ ቀውሶች ውስጥ እንዲሳተፍ እንደሚያስገድዱት ገልጸዋል።
ዘላቂ የምግብ ሉዓላዊነት ለመገንባት በቅድሚያ የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ መረጋገጥ ይገባዋልም ብለዋል።
ትብብሩ ከማንኛውም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ የሆነና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላ የግብርና ምርቶች ፍተሻ ተቋም ሊቋቋም ይገባል ብሎ እንደሚያምን እና ለዚያም እንደሚታገል ገልጸዋል።
