ሁልጊዜ ጅምሯ ብቻ የሚያምረው ሃገራችን፣ በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ ልማቶችም ሆኑ እድገቶች በአያያዝ ጉድለት ፍሬ ሣያፈሩ ቅጠል ብቻ ሆነው የሚቀሩበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ታሪክ ከቀደምት ሀገራት የባቡር ታሪክ ጋር የሚመደብ ሲሆን፣ ከመቶ አመት በፊት ተገንብቶ ለሀገር እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ መጀመሪያ ከጅቡቲ ድሬደዋ በኋላም ወደ አዲስ አበባ የተዘረጋው የባቡር ሀዲድ በጠንካራው መሪ በአጼ ምንይልክ ከተሠሩና ከተሣኩ ዘመናዊ ፈር ቀዳጅ የእድገት መሠረቶች ተጠቃሹ ነው፡፡ በፈረንሣይ መንግሥት የተሠራው የምኒልክ ባቡር ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ሕዝብ፣ ፈሣሽና ደረቅ እቃ በማጓጓዝ የሀገራችን የገቢና የወጪ እቃዎችን በማመላለስ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ አገልግሎት እየሠጠ የነበረ ትልቅ ድርጅት ነበር፡፡
ስለቀድሞው ምድር ባቡር ብዙ የሚፃፍ ታሪክ ያለው ቢሆንም የዛሬው ትኩረታችን በቅርቡ በቻይና ተሰርቶና ተመርቆ ሥራ ስለጀመረው አዲሱ የኤሌትሪክ ባቡር ነው፡፡ ይህ ባቡር በከፍተኛ ወጪ የተገነባ በኤሌትሪክ የሚሰራ ባቡር ሲሆን ሀገራችን ያለባትን የትራንስፖርት (ሎጂስቲክ) ችግር ሊያቃልል የሚችል ትልቅ የሀገር ሀብት ነው፡፡ በአጋጣሚ የቀድሞውን የምኒልክ ባቡር ከተገለገሉት ውስጥ የምመደብ ሲሆን አዲሱንም የኤሌትሪክ ባቡር ለመጠቀም በመቻሌ አምላኬን አመሰግነዋለሁ፡፡
ይህ በቻይና የተሠራው ዘመናዊና ምቹ፣ ከፍተኛ ወጪ የተደረገበት የኤሌትሪክ ባቡር ተሠርቶ ለአገልግሎት መብቃቱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይህ ባቡር ገና ወረቱ ሣያልቅ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ግን በጉዞዬ መታዘብ ችያለሁ፡፡ ከመናገሻ ከተማችን አዲስ አበባ ትልቁ ስቴሽን ለቡ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን የሚያምርና ሁሉም ነገር ተሟልቶለት የተሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን ስቴሽኑ አሁን ያለበት ሁኔታ እጅግ የሚያሳፍር ነው፡፡ ሽንት ቤቶቹ ውሃ የሌላቸው፣ መብራቶቹ ተበላሽተው በጭለማ የተዋጡ አሣፋሪ ስቴሽን ሆኗል፡፡ ልብ በሉ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ላይ ያለው ስቱሽን እንዲህ ከሆነ የሞጆው፣ የአዳማ/ናዝሬቱ፣ የድሬዳዋ-ደወሌው ባቡር እስቴሽ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ እነዚህ በጥሩ ሁኔታ ተሰርተው የነበሩ ሽንት ቤቶችና የእጅ መታጠቢያዎች በሁሉም ስቴሽኖች ተሰባብረውና ተገነጣጥለው ማየት እጅግ ያሳዝናል ፤ያሣፍራልም፡፡ መሥራት ብቻ ሣይሆን የተሠሩትን በተገቢው መንገድ ጠብቆ ማስተዳደር እንዴት ያቅተናል?
ወደ አገልግሎቱ ስንገባ የባቡር ትራንስፖርት በጣም ተመራጭ፣ የተረጋጋና ሠላማዊ፣ ዋጋውም ተመጣጣኝ በመኾኑ በሕዝብ ዘንድ ተመራጭ ነው፡፡ ነገር ግን ባቡር ስቴሽኖቹ ከከተማ ራቅ ያሉ በመሆናቸው ትኬት ለመቁረጥ አስቸጋሪ ኾኗል፡፡ የትኬት መቁረጫዎቹ ማዕከላት በከተሞቹ ውስጥ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ስለባቡሩ አገልግሎትና የጉዞ ፕሮግራም ተገቢ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ይኽ አሠራር ስለሌለ ብዙ ሰው በመጉላላት ላይ ነው፡፡ የትኬት አቆራረጡም ቢሆን በእንከን የተሞላ በመኾኑ በየጊዜው “ትኬት አልቋል” በሚል ሠራተኞች ተመሳጥረው ባቡሩ ውስጥ ትኬት የመሸጥ ተግባሩን አጧጡፈውታል፡፡ በሌላ በኩል የባቡሩ ትኬት የፉርጎና የወንበር ቁጥር ያለው ቢኾንም፣ የባቡሩ አስተናጋጅ ሠራተኞች መንገደኞችን በቁጥጥራቸው መሠረት ማስቀመጥና ሥርዓት ማስከበር ሲገባቸው ከሥርዓተ አልበኞች ጋር በመተባበር አሠራሩ ቅጥ እንዲጣ አድርገውታል፡፡
በሌላ በኩል መንገደኞች ወደ ባቡሩ እስከሚገቡ ድረስ በተዘጋጁት ማረፊያዎች ለረጅም ሰዓታት የሚቀመጡ ሲሆን አጋጣሚውን ተጠቅሞ በድምጽ ማጉያ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንኳን አይሰራም፡፡ ወደ ባቡሩ ሲገባም ቢሆን በሥርዓት ማስተናገድና ስርዓት ማስያዝ ሲገባ የባቡሩ ሠራተኞች እና አስተናጋጆች በራሣቸው ሥራ ተጠምደው ይታያሉ፡፡ ከሁሉ እጅግ የሚያሣዝነው ባቡሩ በየፉርጎ፣ ሽንት ቤትና የእጅ መታጠቢያ ያለው ቢሆንም ይህንን ሽንት ቤት በመቆለፍ “ተበላሽቷል” እያሉ መንገደኛው ለከፍተኛ ሕመምና ችግር እንዲጋለጥ ማድረግ ሃይ ባይ ያጣ አስነዋሪ ተግባር ኾኗል፡፡ ሽንት ቤቶችን በክፍያ ገንዘብ እያስከፈሉ የሚያስጠቅሙ እንዳሉም ታዝበናል፡፡ በዚህ ችግር ምክንያት ወንዶች በሃይላንድ ሽንታቸውን እየሸኑ በየቦታው ለማስቀመጥ ተገደዋል፡፡
በሌላ በኩል ከዚህ በከፍተኛ ወጪ ከተሠራ ባቡር አንዳንድ ተሳፋሪዎች የወንበር ጨርቆችን እያወለቁ መሬት ላይ በማንጠፍ እና ፍራሾችን መሬት ላይ በመጎተት ሲያበላሹት ተው የሚል አካል አለመኖሩንም ተመለክተናል፡፡ ባቡሩ ምግብ የሚበላበት ካፌ ያለው ቢሆንም የካፌው ወንበሮች ላይ በመተኛት አገልግሎት የሚያደናቅፉ ግለሰቦችን የባቡሩ አስተናጋጆች ተባባሪ በመኾን በዝምታ ሲያልፉ አይተናል፡፡ እነዚህ ሠራተኞች ለማበላሸት የተቀጠሩ እስከሚመስሉ ድረስ የሚታየው ሥርዓት አልበኝነት በእጅጉ ይዘገንናል፡፡
በሌላ በኩል የባቡሩን ደህንነት ለማስጠበቅ የፌደራል ፖሊሶች አብረው የሚጓዙ ቢሆንም፣ በርካታ ባቡሮች በተለያየ ጊዜ እና ቦታ መስታወታቸው በድንጋይ ተመትቶ ተበሣስቶ ይታያል፡፡ ሌላው እጅግ አሣሳቢው ነገር የባቡሩ ሃዲድ የተሠራበት ብሎን እየተፈታ መወሰዱ ነው፡፡ ይህ በሃዲዱ ላይ እየተካሄደ ያለው የብሎን መፍታት ዘመቻ በቀላሉ ሊታይ የሚገባው ወንጀል አይደለም፡፡ እነዚህ ዘራፊዎች በተለያየ ጊዜ ብሎን ሲፈቱ የተያዙ ቢሆንም ከሳሽ ባለመኖሩ ፖሊስ ወዲያው እንደሚለቃቸው ይነገራል፡፡ ይህ የሚያሣየው ድርጅቱ ያለበትን ትልቅ ክፍተት ሲሆን በፌዴራል ፖሊስ ቅኝትና ጥበቃ እየተደረገ መኾኑ ብቻ አስተማሪ ቅጣትና እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ ሊቆም እንደማይችል ነው፡፡
በአጠቃላይ ይህን ትልቅ ድርጅት መንግሥት በአስቸኳይ ሊመለከተውና ሊፈትሸው፣ እርምትም ሊያደርግ ይገባል፡፡ መንግሥት ስለልማትና ስለእድገት በየዕለቱ እየተናገረ በተግባር ግን በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የሀገርና የሕዝብ ሃብቶች በተገቢው መንገድ ተጠብቀው ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሠጡ ማድረግ ካልተቻለ የያዝነው መንገድ የእድገት ሣይሆን የውድቀት መኾኑ አጠራጣሪ አይኾንም፡፡ በሌላ በኩልም እንዲሁ እንደ ሕብረተሰብ ሁልጊዜ እድገት እየናፈቅን እና የውጪውን እያደነቅን ኖረን፣ እድገቱና ቴክኖሎጂው ወደሀገራችን ሲመጣ ግን የራሳችን ሃብት መኾኑን ተገንዝበን፣ አስተሣሰባችን ከቴክኖሎጂው ጋር በማዘመን ልንገለገል ይገባል፡፡ መሠልጠን የሚጀምረው ከራስ ነውና፡፡
በተለይ ከፍ ብዬ ባነሳሁት ሥርዓት አልበኝነት ላይ ወጣቱ ሠፊውን ድርሻ ስለሚይዝ በአለባበሳችሁ የሠለጠናችሁ የምትመስሉ ተግባራችሁ ሲታይ ግን ከሥልጣኔ የተጣላችሁት፣ የዛሬን ብቻ የምታስቡ ወጣቶች ቆም ልትሉ እና ረጋ ብላችሁ ልታስቡ ይገባል፡፡ ሁሉን ነገር በተቀመጠው ሥርዓት፣ ቦታና ጊዜ ለመተግበር አእምሮአችንንና አካላችንን እናሰልጥነው፡፡ ሥርዓተ አልበኞችን መታገል እንጂ መተባበር አይገባም፡፡ መንግሥት ዋናው ተግባሩ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ነውና ይህንን በአፋጣኝ በመተግበር አንጋፋውን ተቋም ይታደገው እላለሁ፡፡
