መ/ር ጌታቸው በቀለ
ቅዱስ ያሬድ በድጓው የዐቢይ ጾምን መካከለኛ (እኩሌታ) ሳምንት እሑድ የጌታችን ዳግም ምጽአት መታሰቢያ አድርጎ “ደብረ ዘይት” በማለት ሰይሞታል፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የደብረ ዘይት በዓል የጌታችን ዳግም ምጽአት፣ የዓለም ፍጻሜ ጉዳይ የሚሰበክበት እና የሚተነተንበት በዓል ነው፡፡
ይህም የተደረገው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ እና ስለ ዳግም ምጽአቱ ስላስተማራቸዉ በጌታችን ትምህርት መሠረት ነገረ ምጽአቱን (የመምጣቱን ነገር) እያሰብን እንድንዘጋጅ የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍም የደብረ ዘይትን ታሪካዊ ዳራና የክብረ በዓሉን ምንነት እንመለከታለን፡፡
ደብረ ዘይት
ደብረ ዘይት የሚለው ከሁለት ጥምር ቃላት የተገኘ ነው፡፡ ይኸውም፡- “ደብር” እና “ዘይት” ማለት ነው፡፡ ማለት ነው፡፡ “ደብር” ማለት “ተራራ” ማለት ሲሆን “ዘይት” ማለት ደግሞ “ወይራ” ማለት ነው። ስለዚህ “ደብረ ዘይት” የሚለው በአንድነት ሲነበብ የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ የወይራ ተራራ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ደበረ ዘይት የወይራ መብቀያ፣ በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው።
ደብረ ዘይት (Mount of Olives) የወይራ ዛፍ የመላበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ስያሜውን ያገኘው በተራራው ላይ በብዛት ከሚገኘው የወይራ ዛፍ ነው፡፡ ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ 75 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲኾን፤ ከባሕር ጠለል በላይ 800 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ /የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት፤ሥርዐት አምልኮትና የውጭ ግንኙነት፤ ገጽ 73/፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገለጸው ደብረ ዘይት ከቤተ ፋጌና ከቢታንያ ተራራ እንዲሁም ከጌቴሰማኒ ከሌሎች የኮረብታማነት ምልክት ከሚታይባቸው አቀበቶች በስፋቱና በግዝፈቱ የሚለይና ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የቄድሮስ ሸለቆ ተሻግሮ የሚገኝ ተራራ ነው “ዳዊትም ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት አቀበት ወጣ፡፡” እንዲል /፪ኛ ሳሙ. ፲፭፥፴/፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ 1972ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ 215/፡፡ ደብረ ዘይት ተራራ (Mount of Olives) በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ከሠራባቸው ቅዱሳት መካናት አንዱ ነው፡፡ ታላላቅ ምስጢር የተከናወነበት፣ ለደቀመዛሙርቱ ትምህርት የሰጠበት፣ ስለ ምስጢረ ምጽአቱ ያስተማረበት፣ ያረገበትና ዳግመኛ ለፍርድ የሚመጣበት በኢየሩሳሌም የሚገኝ ተራራ ነው፡፡
የደብረ ዘይት ስያሜዎች
ደብረ ዘይት ወይም አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ሌሎች ስያሜዎችም አሉት። በተጨማሪ ዳግም ምጽዐት፣ የፍርድ ቀን፣ የጌታ ቀን፣ ሕልቀተ/ሕልፈተ ዓለም፣ ዕለተ ፍዳ፣ ዕለተ ደይን ዳግመኛ ልደት ትንሣኤ ዘጉባኤ በመባል በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ይጠራል።
ደብረ ዘይት ተራራና ታሪካዊ ክስተቶቹ
ደብረ ዘይት (Mount of Olives) ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችና ያስተናገደ ተራራ ነው፡፡ ዳዊት ከአቤሴሎም ጋር በተጣላና በኮበለለ ጊዜ፤ ይህንን ግዙፍ ተራራ አቋርጦ ሔዶ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳናል /፪ኛ ሳሙ.፲፭፥፴/፡፡
መድኃኔ ዓለም ክርስቶስም አዳምን ከነልጆቹ ሊታደግና ለዓለም ቤዛ ሊሆን ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ቀን ቀን ሲያስተምር ውሎ ማታ የሚያድረው በደብረ ዘይት ተራራ በሚገኘው ዋሻ ነበር “ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር”/ሉቃ.፳፩፥፴፯/፡፡ዓባይነህ ካሤ (ዲ/ን)፤የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት(ሁለተኛ መጽሐፍ)፤1994ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ገጽ 75/፡፡
በዕለተ ሆሣዕናም ከኢየሩሳሌም ሲወጣ የገባው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ነው/ማር.11፣1/፡፡ የአብ የባሕርይ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ እጅ ተይዞ ወደ ፍርድ አደባባይ ያመራውም ደብረዘይት ግርጌ ሥር ከሚገኘው የጸሎት ሥፍራው ጌቴሴማኒ ጸሎቱን ከፈጸመ በኋላ ነው /ማቴ.፳፮፥፴/፡፡
በዚህ ዓለም አገልግሎት ፈጽሞ ለሰው ልጅ ክብርና ነጻነትን ካጎናጸፈ በኋላም ያረገውም በዚሁ በደብረ ዘይት ተራራ ነው /ሉቃ.፳፬፥፶፩/:: ከሁሉ በላይ ግን አዳምን ነጻ ካወጣውና ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶ ካረገ በኋላ ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስና ስለ ዳግም ምጽአት (ነገረ ምጽአት) ያስተማረው በዚሁ ተራራ ላይ ነው/ማቴ.፳፬፥፫፤፳፭፥፴፩-፵፮፤ ማር.፲፫፥፫/፡፡
ወደፊት ዓለሙን ለማሳለፍ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ትንቢት በመጨረሻይቱም ሰዓት በፍርድ አደባባይ ሲቀመጥ ዙፋኑን የሚዘረጋው በዚሁ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ መሆኑን ነቢዩ አስረግጦ ጽፏል“በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ፤ ደብረ ዘይትም በመካከል ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፤እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል፤የተራራውም እኩሌታ ወደ ሰሜን፣እኩሌታውም ወደ ደቡብ ይርቃል” /ዘካ.፲፬፥፬/፡፡ /መለከት 15ኛ ዓመት ቁ.3፤ መጋቢት 1999 ዓ.ም፤ ገጽ 9 ጥራዝ መጋቢት 1997-2ዐዐዐ/::
በዚህ ዕለት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም መምጣት ነገረ ምጽአቱ ይነገርበታል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በትንቢቱ እግዚአብሔር በግልጽ ይመጣል ብሎአል/መዝ.፵፱፥፪/፡፡ ራሱም ክርስቶስ ባስተማረው ወንጌል /ማቴ.፳፬፥፳፯/ “እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፡-ንገረን ይህ መቼ ይኾናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት፡፡
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች፡- እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡ ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፣አትደንግጡ፤ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው” በመጣም ጊዜ ይህን ዓለም ከመኖር ወደ አለመኖር አሳልፎ ሐዲሱን ሰማይና ሐዲሱን ምድር ወርሰን እንድንኖር ያደርጋል /፪ኛ ጴጥ.፫፥፲፫/፡፡ ሐዲስ ሰማይና ሐዲስ ምድር የተባለች ፍጻሜ የሌላት ዘላለማዊት መንግሥት እንደሆነች እንገነዘባለን፡፡ /ትንሣኤ፤መጋቢት 1978 ዓ.ም ፤ቁ 1ዐዐ ፤ገጽ 12/፡፡
የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ
ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ “የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብለው ሐዋርያቱ ለጠየቁት ታላቅ ጥያቄ በስፋትና በጥልቀት ትምህርት የሰጠበት ክፍል የሚሰበክበት ዕለት ነው፡፡ /ማቴ.፳፬፥፩—፴፮/
ጌታችን ስለ ዳግም ምጽአቱ ባስተማረው ትምህርት ዘመኑ ሲቃረብ የተለያዩ ተፈጥሮአዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ምልክቶች እንዲሚከሰቱ ተናግሯል፡፡ የሚመጣበትን ዕለቱንና ሰዓቱን ሳይሆን ምልክቶችን ነገረን፡፡ እነዚህም ምልክቶች አብዛኞቹ በዘመናችን እየተፈጸሙ ሲሆን፤ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ ምን ማድረግ እንደሚገባንም ምክሮችን ሰጥቶናል፡፡ እነዚህም፡-
ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ
“ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉና እንዲል” እኛም ከሐሰተኞች ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ሐሰተኞች በእርሱ ስም ወይም በቅዱሳን ስም የበግ ለምድ ለብሰው በጎችን ለመንጠቅ ሲመጡ እኛም በእነርሱ እንዳንነጠቅ እንድንጠነቀቅ ይህንን ማስጠንቀቂያ ሰጠን፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች በመምሰል ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን አሠራራቸው ሐሰተኛነታቸው ይገለጣል፡፡
በሐሰተኞች ወሬ ልባችሁ አይታወክ
“ማንም ክርስቶስ በዚህ አለ ወይም በዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፡፡ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሀሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና፡፡ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ፡፡ አስቀድሜ ነገርኳችሁ፤ በበረሓ ነው ቢሏችሁ አትውጡ፤ በእልፍኝም ነው ቢሏችሁ አትመኑ” በማለት የትንቢቱ መፈጸሚያ እንዳንሆን እንድንጠበቅ አስጠንቅቆናል፡፡ እኛ ግን በሐሰተኞች ማጭበርበር ሳንደናገር እውነት የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይዘን የክርስቶስን መገለጥ በተስፋ እንድንጠብቅ ታዘናል፡፡
ትንቢቱ ሊፈጸም የግድ ነውና አትደንግጡ
የታየው ምልክቱ እንጂ መጨረሻው አይደለምና አትደንግጡ፡፡ ጦርንም የጦርንም ወሬ ስትሰሙ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ ሲነሳ ስታዩ፣ ረሀብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ ሲሆን አትደንግጡ፡፡ ይህ መጀመሪያው እንጂ መጨረሻው አይደለምና! ይህም ሁሉ ሊሆን የግድ ነውና አትደንግጡ፡፡
አለመደንገጥ ነገሮችን በጥሞና ለመመርመር ይጠቅማልና “አትደንግጡ” አለን፡፡ መደንገጥ፣ መረበሽ መፍትሔ አይሆንምና፤ እነሆ አስቀድሞ ተነግሮናልና ምልክቶቹ ሲፈጸሙ መደንገጥ የለብንም፡፡ ይልቁንስ እንደ ደጋግ አባቶቻችንና እናቶቻችን የአቅማችንን አድርገን እንደበጎ አገልጋይ በጌታ ምጽአት ለመመስገን፣ ክብርን ለማግኘት እንትጋ፡፡
የጥፋትን ርኩሰት በተቀደስው ስፍራ ስታዩ ቀኑ እንደቀረበ አስተውሉ
ምልክቶቹ ሲታዩ ጊዜው እንደደረሰ አስተውሉ፡፡ ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፡፡ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲሁ እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ሲታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ፡፡
ምልክቶቹ ሲታዩ መስማትና ማየት ብቻ ሳይሆን ማስተዋልም እንደሚገባ ይህንን አስተማረን፡፡ የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ስናይ እንድናስተውል፣ በንስሐም እንድንመለስ ታዘናል፡፡ በተቀደሰው ስፍራ፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት ከጥፋት ርኩሰት ልንርቅ፣ የቀረቡትንም በትምህርትና በተግሳጽ ከጥፋት ልናርቃቸው ይገባል፡፡
እስከመጨረሻው የጸና ይድናል
ለመከራ አሳልፈው ሲሰጧችሁ፣ ሲገድሏችሁ፣ ስለ ስሜም የተጠላችሁ ስትሆኑ በእምነታችሁ ጽኑ፡፡ ብዙዎች ሲሰናከሉ፣ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ሲሰጣጡ፣ ከአመጻም ብዛት የተነሳ ፍቅር ስትቀዘቅዝ በእምነታችሁ ጽኑ፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በጊዜውም ያለጊዜውም ጽና›› ያለው ለዚህ ነው (2ኛ ጢሞ 4፡2)፡፡ በዚህ ወቅት መከራን መታገስ፣ አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ መስዋዕትነትን በመክፈል ጽናትን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ
ክረምት የቡቃያ እንጂ የፍሬ ዘመን አይደለምና በሃይማኖት ብቻ ሳላችሁ ምግባርን ሳትሠሩ ሞት እንዳይታዘዝባችሁ ጸልዩ፡፡ ሰንበትም ዕለተ ዕረፍት ናትና በዕረፍት ሳላችሁ ሞት እንዳይታዘዝባችሁ ጸልዩ፡፡ በሃይማኖት ሳላችሁ ምግባር ሳይኖራችሁ ብትወሰዱ መጨረሻችሁ መከራ ይሆናልና ጸልዩ፡፡
ክረምትና ሰንበት ለሽሽት አይመችም መንገድና አቅጣጫ የሚያሳይ የለምና፡፡ መንፈሳዊ ምግባራትን መሥራት የማንችልበት ጊዜ ሳይመጣ፣ በጉብዝናችን ወራት እምነታችንን አጽንተን፣ ጠብቀን፣ በጎ ምግባራትን ሠርተን ጌታችን ሲገለጥ በምግባራቸው ከሚያመሰግናቸው ቅዱሳን ጋር ለመቆም ልንተጋ ያስፈልጋል፡፡
የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም እና ለአርዓያነት በተገለጠ ጊዜ አመጣጡ በአጭር ቁመት እና በጠባብ ደረት ተወስኖ በትሕትና ነበር፡፡ ዳግመኛ የሚመጣው ግን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ብሎ አስተማረን፡፡ ያቺን ቀን ከእርሱ በቀር የሚያወቃት የለም፡፡
በኖኅ ዘመን እንደነበረው የእርሱም መምጣት እንደዚያ ይሆናል፡፡ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃና ቤቱን በጠበቀ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወው ነበር፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና፡፡ ይህ ቀን ስለማይታወቅ ሁል ጊዜ በንስሐ እና በሥጋ ወደሙ ተዘጋጅተን ልንኖር ይገባናል፡፡
ከላይ የተገለጹት ማስረጃዎች የሚያመለክቱት የደብረ ዘይትን ተራራ ምንነትና በደብረ ዘይት ተራራ ላይ የተከናወኑትን ተግባራት፤ ወደፊትም ልዑል እግዚአብሔር በግርማ መንግሥቱ ለፍርድ በሚመጣበት ወቅት፤ ዙፋኑን የሚዘረጋው በዚሁ ቅዱስ ተራራ ላይ መሆኑን የዳግም ምጽአቱን ምስጢር የሚገልጥበት መሆኑን የሚያጠይቅ ነው፡፡
በዓለ ደብረ ዘይት አከባበር በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የዐቢይ ጾም እኩሌታ በሚውለው እሑድ፤ አምስተኛው ሳምንት በሚውለው የደብረ ዘይት በዓል በደመቀ ሁኔታ ሲከበር ይኖራል፡፡ በዚህ ዕለት ማኅሌቱ፣ ቅዳሴው አገልግሎቱ ሁሉ ከዚሁ በዓል ጋር ተዛማችነት ያለው የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ነው፡፡ /መለከት መጽሔት፤ 14ኛ ዓመትቁ 3፤ መጋቢት 1998 ዓ.ም፤ ገጽ 9-1ዐ/፡፡
ደብረ ዘይት ተጽፎና ተተርጉሞ የማያልቅ ሰፊ፣ ጥልቅና ምጡቅ ትምህርትን የያዘ በዓል ነው። በዓሉ በቃለ እግዚአብሔርና በትምህርት የሚታሰብ ከመሆኑም በተጨማሪ በምእመናኑ ዘንድ ጌታችን በዳግም መጽአት የሚጠይቃቸውን የምግባር ጥያቄዎች ግምት ውስጥ ያስገቡ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡
ይኸውም ዳቦውን፣ ቆሎ ቀልተው ንፍሮውንና የመሳሰለውን አዘጋጅተው ድኾችን ይመግባሉ፤ ከልብሶቻቸውም ጥቂቶችን እያወጡ ይመጽውታሉ፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ይህ በዓል በሀብታሙም በድኻውም፣ በትልቁም በትንሹም ዘንድ በበጎ ሥራ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ተከብሮና ታስቦ ይውላል።
ሕዝበ ክርስቲያኑ ያለውም የሌለውም ቤት ያፈራውን ምግብ ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣና ከመንፈሳዊ አገልግሎት በኋላ አስቀድሞ ድሆችን በመጎብኘት፣ በመመገብና በማጽናናት ከደሆች የተረፈውን እርስ በእርስ በመገባበዝ፣ የተጣላ በማስታረቅ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ከዋርካውና ከፅዱ ሥር ዐርፎ ይውላል። ይህ ሁሉ ምጽአቱን በተግባር የማሰብ አከባበር ነው፡፡ ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፤ በዓላት፤ 1999ዓ.ም፤ ገጽ 100፡፡ በሀገራችን ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ አቅጣጫ በዚህ ስም የሚጠራ ቦታ ይገኛል፡፡
እንደ ማጠቃለያ
ደብረ ዘይት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዘወተረበት ከመሆኑም በላይ ስለ ምስጢረ ምጽአቱ ያስተማረበት፣ ያረገበትና ዳግመኛ የሚመጣበት በመሆኑ፤ ቅዱስ ያሬድ በድጓው የዐቢይ ጾምን መካከለኛ እሑድ የጌታ ዳግም ምጽአት መታሰቢያ አድርጎ ደብረ ዘይት በማለት ሰየመው፤ በጾመ ድጓውም በዚሁ ዕለት የምጽአቱን ቃለ እግዚአብሔር ሠራ፡፡ /የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000ዓ.ም፤ ገጽ 48/።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱ ደብረ ዘይት ነው፡፡ የደብረ ዘይትን በዓል በየዓመቱ ስናከብር አጽንኦት ሰጥተን ማስተዋል ያለብን ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው ለጻድቃን የዘላለም ሕይወትን፣ ለኃጥአን ደግሞ ፍርድን ሊሰጥ መሆኑን ነው፡፡ የመምጣቱና የዓለም መጨረሻ ምልክቶች ሲከሰቱ እንድንጠነቀቅ፣እንዳንደነግጥ፣እንድንጸና፣እንድንጸልይ፣ እንድንጠበቅ፣እንድናስተውልና እንድንዘጋጅ ራሱ ባለቤቱ መክሮናል፡፡
የእግዚአብሔር ጥሪ ሁሉም የአዳም ዘር መንግሥቱን እንዲወርሱ ነው፤ እኛንም በቀኙ ያቆመን ዘንድ “የአባቴ ቡሩካን ኑ ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ” የሚለውን የሕይወት ቃሉንም ያሰማን ዘንድ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዋቤ መጻሕፍት
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን እምነት፣ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት፤
✍️ ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፤
✍️ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም፤
✍️ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አንደኛና ሁለተኛ መጽሐፍ፤
✍️ ባሕረ ሐሳብ፤ የዘመን ቆጠራ ቅርሳችን ከታሪክ ማስታወሻ ጋራ፤
✍️ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ
✍️ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት
✍️ በዓላት ለምን? እንዴት?
✍️ መለከት መጽሔት
✍️ Encylopedia of Aethiopica
