ደጆችሽ አይዘጉ ማኅበር ዋነኛ ዓላማው የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን አስከፍቶ አገልግሎት በማስጀመር ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ሲሆን አገልግሎቱን ለማከናወን በርካታ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
አቶ ሙሉጌታ ተገኘ የደጆችሽ አይዘጉ ጠቅላላ ማኅበር የአዲስ አበባ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ማኅበሩ ከምሥረታው ጀምሮ በቁጥር ከ139 በላይ የሆኑ በሀገራችን የገጠር ክፍሎች የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን የማስከፈት ሥራዎች በመሥራቱ አገልግሎት ጀምረዋል ብለዋል፡፡
አክለውም ከማስከፈት ተግባራት በሻገር ከ54 ሺህ ብር በላይ በማውጣት ለተለያዩ አድባራት እና ገዳማት አገልጋዮች ወርኃዊ ደሞዝ ክፍያ መፈጸሙን እንዲሁም ለአብነት ትምህርት ማስኬጃ ከ19 ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በማኅበሩ የሐዋርያዊ ተልዕኮ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ወንድይፍራው በበኩላቸው በቅርቡ በ3 ወረዳዎች የአካባቢያቸውን ቋንቋ የሚችሉ፣በምእመናን እና በካህናት መካከል ያለውን የቋንቋ ችግር የሚፈቱ፣ባሉበት በቀዬአቸው የሚያገለግሉ የ60 ካህናት ሥልጠና እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡
አንድ የሆነው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲሳካ በገቢ አቅማቸው የጎለበቱ በከተማ ያሉ አድባራት በገጠር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን በመደገፍ ረገድ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ አሳስበዋል፡፡
©ማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት
