ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ምርትና አገልግሎት የሚያስተዋወቅ ‘ቪዚት ኢትዮጵያ’ የተሰኘ የግብይት መተግበሪያ ይፋ ሆኗል።
መተግበሪያው በዘርፉ ያሉ ተዋንያንን አንድ ላይ የሚያገናኝ ሲሆን መረጃ ላይ የተመሰረተ ግብይት ተግባራዊ በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል እንደሆነ ነው የተመላከተው።
ከዚህ ባሻገር ቱሪስቱ ያለውን ግብረመልስ ለመቀበል የሚያስችል ፤ በርካታ ሆቴሎች የዋጋ ቁርጣቸውን የሚያቀርቡበትና የአስጎብጂ ድርጅቶች የጉዞ ጥቅሎች የሚገኝበት እንደሆነ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።
አክለውም ጎብኚዎች ይዘው ለሚመጧቸው ዕቃዎች ከጉምሩክ ኮሚሽን አስቀድመው ፍቃድ ማግኘት የሚችሉበት መሆኑን አስረድተዋል።
ሀገሪቱ ያላትን የቱሪዝም አቅም ለመጠቀም የዲጂታል መሰረተ ልማት አስፈላጊነት ሌላው አፅንዖት የተሰጠበት ጉዳይ ነው።
መተግበሪያው ላይ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች የተመዘገቡ ሲሆን በቀጣይ ሁሉም የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ተዋንያን በዚሁ ‘ፕላትፎርም’ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡
መተግበሪያውን የመረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደርና የቱሪዝም ሚኒስቴር በጋራ አልምተውታል።
