የቴክኖሎጂው ግዙፍ ኩባንያ ጎግል አማርኛን፣ አፋን ኦሮሞን እና ሱማልኛን ጨምሮ 13 የአፍሪካ ቋንቋዎችን በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የፍለጋ አገልግሎቱ ውስጥ ማካተቱን ይፋ አድርጓል።
በኩባንያው የ’ዋክሳል’ ፕሮጀክት አማካኝነት እውን የሆነው ይህ ዝመና፣ ‘AI Overviews’ እና ‘AI Mode’ የተሰኙ መተግበሪያዎች በአህጉሪቱ ቋንቋዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል።
በዚህም ተጠቃሚዎች ስለፈለጉት ጉዳይ በራሳቸው ቋንቋ አጭር ማጠቃለያዎችን ማግኘት፣ በጽሑፍ፣ በድምፅ ወይም በምስል ጥያቄዎችን በማቅረብም ጥልቅ ምላሾችን ማግኘት ይችላሉ።
የጎግል ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ካቤሎ ማክዋኔ እንደገለጹት፣ ይህ እርምጃ ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ብቻ ተወስኖ የሚፈጥረውን መገለል በመቅረፍ አፍሪካውያን የዲጂታል ኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑና ማኅበረሰባዊ ችግሮቻቸውን በፈጠራ እንዲፈቱ ያግዛቸዋል።
ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች በተጨማሪም እንደ ስዋሂሊ፣ ዮሩባ እና ዙሉ ያሉ ቋንቋዎች በዚህ ታሪካዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር ውስጥ መካተታቸው ተገልጿል።
