በትግራይ ክልል እየታየ ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሕብረት ከፖለቲካዊ ፍላጎቶች ይልቅ ለሕዝብ ደህንነትና ለአገር ሕልውና ቅድሚያ እንዲሰጥ አሳሰበ።
የሕብረቱ ስትራቴጂክ አማካሪ አቶ ያሬድ በረኸ እንደገለጹት፣ በክልሉ ያለው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎልና የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ እስከ 420 ብር መናር፣ እንዲሁም የባንክ አገልግሎት እጥረት ማኅበረሰቡን ለከፋ አለመረጋጋት ዳርገውታል። የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ውስንነትም የችግሩን ጥልቀት አባብሶታል።
በመሆኑም የፌደራል መንግሥት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ሕወሓት ልዩነቶቻቸውን በሰከነ መንፈስ በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት የጦርነት ጉሰማ እንዲያቆሙ ጥሪ ቀርቧል።
በተለይም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር፣ የክልሉ የግዛት አንድነት እንዲከበርና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ሕብረቱ ግፊት እያደረገ ይገኛል።
እነዚህ መሠረታዊ የሰላም ነጥቦች አለመፈጸማቸው ለዳግም ግጭት አዝማሚያ መንስኤ እየሆኑ በመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሕዝቡን የሰላም ፍላጎት በማስቀደም በኃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱ ተጠይቋል።
