በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል #ጂንካ ከተማ በተከሰተው ማርበርግ ቫይረስ አንድ ተጨማሪ ሰው መያዙን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ፣ ትላንት ህዳር 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ዘጠኝ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ አንድ ሰው በቫይረሱ መያዙን ማረጋገጡን ገልጿል።
በዚህም አጠቃላይ በማርበርግ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4 ደርሷል ብሏል። የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ የቫይረሱ ምልክት ታይቶባቸው ህይወታቸው ካለፈ ስድስት ሰዎች መካከል ሦስቱ ሰዎች የሞቱት በቫይረሱ መሆኑን ህዳር 8 ቀን በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የ #አሜሪካ መንግስት ዝግጁ መሆኑን አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ይህን የገለጹት፣ በኢትዮጵያ በተከሰተው የማርበርግ የቫይረስ በሽታ አጠቃላይ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት ዙሪያ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጋር ትላንት በተወያዩበት ወቅት ነው።
ዶ/ር መቅደስ የበሽታውን የላብራቶሪ ምርመራ፣ ከታማሚዎች ጋር የነበሩ ንክኪዎች ክትትል፣ የአደጋ ዝግጁነት እና የማህበረሰብ ተሳትፎን ጨምሮ አስቀድመው የተተገበሩ ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን አብራርተዋል ተብሏል።
