“እንደ ሙሴ እኛን የሚጠቅም ሌሎችን የማይጎዳ ሀሳብ ይዘን መምጣት ይኖርብናል። “ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መልአከ
ለምን ፈራን?
ፍርሃት ወይስ ትዕግሥት?
ከዚህ ዝምታ ጀርባ ያለው ነገር ምንድነው?
ፍርሃት?፣ ትዕግሥት?፣ ተስፋ?፣ የሀገር ፍቅር? ምንድነው ያለው?
መከራን ተላምዶ መኖር ለእስራኤል ነጻነትን አላመጣላቸውም። የአስገባሪዎቻቸውን ጭቆና መታገሣቸው ፍቅርን አላተረፈላቸውም። ስቃያቸው በበዛ ቁጥር አስገባሪዎቻቸው ደስ እያላቸው መጣ።
ዝቅ ባሉላቸው ቁጥር እርግጫውን ጨመሩባቸው እንጂ ዝቅታቸው ምሕረትን አላስገኘላቸውም።
ለፈርዖን ጽኑ ጽኑ ከተሞች ፊቶምና ራምሴን ቢሠሩለትም ፈርዖን ያንን አይቶ እንደ አንድ ግብጻዊ በሠሩት ከተማ በክብር እንዲኖሩ አልፈቀደላቸውም።
ይልቁንም ጉዳዩ ከፍ እያለ መጣና ወንድ ልጅ የወለደች ሴት የወለደችውን ልጇን በዐይኗ ሳታየው ምጧ ሳይለቃት፣ ደ*ሟ ሳይቆምላት ከእናቱ ማኅፀን ተቀብለው በባሕር የሚጥሉ አዋላጆችን ሾመባቸው።
ግፍ የለመደ ግፍን አይጠግብም። ሰውን መ*ግ*ደ*ል የለመደም ሰውን ማዳን አይወድም። በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ የሚያልፈው እስራኤል ከዮሴፍ ሞ*ት እስከ ሙሴ ልደት እንኳን ብንመለከት ለ279 ዓመታት ይህንን ሁሉ መከራ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ሲያልፉት ኖሩ እንጂ ምንም ስለማለታቸው መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም።
መከራን የሚያደርሱባቸው ግብጻውያን በሰላም እየኖሩ መከራን የሚቀበሉ እስራኤላውያን በሰቀቀን ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ያስመርሯቸው ነበር” ስለሚል።
እኛም እንዲሁ ሆነናል!
ስማችንን ሲያጠፉት ዝም ስንል ሕይወታችንን ማ*ጥ*ፋ*ት ጀመሩ። ያንጊዜ በየመድረኩ ቤተ ክርስቲያናችንን ስሟን የሚያጠፉ ሰባኪዎችን አሠማርተው ሲሰብኩ ብንቃወም ኖሮ የዛሬውን መከራችንን ያንጊዜ ማስቆም እንችል ነበር።
በጣም የሚያሳዝነው ያንጊዜም ዛሬም የምናደርገው ተቃውሞ ተመሳሳይ ነው። ያንጊዜም አንዳንድ ግለሰቦች ወይም ማኅበራት ካልሆኑ በቀር አጥፊውን ትርክት ለመቃወምና ለማስቆም ከሚመለከተው የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ከላይ ወደታች ወርዶ የተሠራበት መመሪያ አልነበረም (እኔ አላውቅም)።
ነገር ግን ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቶ ምዕመናንና ካህናትም ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያንን በስሟ እንድትጠራ አድርገን ቢሆን ኖሮ ዛሬ በቦታችን መኖር እንችል ነበር።
ያንጊዜ ትክክለኛ ታሪኳ ብቻ ይነገር ብለን ቢሆን ኖሮ ዛሬ የሚገባንን ክብር እናገኝ ነበር። ይኸው ውጤቱ ስማችንን በማጥፋት የጀመሩትን ዘመቻ ሕይወታችንን በማጥፋት አሳዩን።
መጀመሪያ ከታሪክ መጽሐፍ ላይ የፋቋትን ቤተ ክርስቲያን ከምድር ላይ ማጥፋት አይከብዳቸውም።
ግን እኛ በዚህ ልክ ለምን ፈራን?
የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ዕቅዳቸውን ከነገሩን ሰንብተዋል፤ ደሴ ገብርኤልን መስጊድ እንደሚያደርጉት፣ “አላሁ አክብር” እያሉ ወገኖቻችንን በ*እ*ሳ*ት እ*ያ*ቃ*ጠ*ሉ ቪዲዮ ካሳዩን፣ ለሁለት ስንከፈል፣ በምድር ላይ ስንበተን በራእይ እንደተመለከቱ ከነገሩን ስንት ዓመት ሆነው እኮ!
የት አለ እኛ የሠራነው ራስን የማዳን ሥራ?
በጣም ራስ ወዳዶች ሆነናል፤ ምቾትና መቀማጠል ከክርስቶስ ፍቅር የለየውን አገልጋይ ስለቤተ ክርስቲያን መከራ ይቀበላል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው።
ሐዋርያት “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?” ብለው የተናገሩት አስቀድመው ልቡናቸውን በክርስቶስ ፍቅር ከዓለም ለይተዉት ስለነበር ነው። እኛ ግን ሳንዋሽ እንናገር ካልን የከበደን ነገር ከዚህ ዓለም ፍቅር መለየት ነው። ዓለምን የሚወድ ሰው ፈሪ ነው። ሀብቱ ይታገድበታል፤ ሹመቱ ይቀርበታል፤ በሚስቱ፣ በልጆቹ ያመካኛል።
አሁን ከዚህ ፍርሀት እንውጣ። አስተውሉ! የእስራኤል ዝምታ ፈርዖናውያንን አላራራቸውም። ራስህን ካላስከበርህ ከተማውን ብቻህን ስትገነባው ቢያዩህም ሠርተህ ስትጨርስ በስማቸው ያስመዘግቡታል።
መጀመሪያ ክብርህን አስጠብቅ። ከዚያ ሥራህን ቀጥል።
ቢዘገይም ዛሬ ከተጀመረ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። እስራኤል ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ቢዘገዩም በመጨረሻ ለውጥ የመጣው ሙሴ ፊት ለፊት ከፈርዖን ጋር ከተከራከረ በኋላ ነው።
ሙሴ ግብጽን የማይጎዳ እስራኤልን ግን የሚጠቅም ሀሳብ ይዞ ነው የመጣው። እኛ አሁንም እንደ ሙሴ እኛን የሚጠቅም ሌሎችን የማይጎዳ ሀሳብ ይዘን መምጣት ይኖርብናል።
ቤተ ክርስቲያኒቱን እንድትመሩ መንፈስ ቅዱስ የሾማችሁ አባቶቻችን እባካችሁ ቀድማችሁ ለሚፈስሰው የክርስቲያኖች ደም ዋጋ ስጡና ተነጋገሩበት፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚጠቅም ሌሎችን ኢትዮጵያውያን የማይጎዳ ስልት አምጡ።
ሕዝቡ እናንተን እየጠበቀ እስከ መቼ ያልቃል? አርባና አምሳ ሰው በአንድ ጉድጓድ ከመቅበር ወዲያ ምን ሊመጣ?
መንግሥት ሞ*ቱ የተመቸን መስሎት ከሆነ እንዳልተመቸን ንገሩልን፤ ሕዝቡ ሲያልቅ እናንተን ሊያርዱ እንደሚመጡ አታውቁምን?
ሕጻናትን ሲ*ያ*ር*ዱ የማይራሩ ጨካኞች እናንተን የሚያከብሩ ይመስላችኋል?
በፍጹም!
የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ተጠብቆ የሚኖረው ዛሬ ያሉ የሲኖዶሱ አባላት ቤተ ክርስቲያኒቱን አስከብረው ሲያልፉ ነው።
ካልሆነ ግን ሲኖዶስን የማያውቅ ትውልድ ይፈጠራል። በታዋቂ ግለሰቦች፣ በሕይወታቸው ቆርጠው መናገር በጀመሩ ሰባኪዎች፣ ማኅበራት ከተከፋፈለ በኋላ አባቶችን ለመስማት ይቸገራልና ዛሬውኑ ቅዱስ ሲኖዶስ እርምጃ ቢጀምር ብየ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን ልጅነቴ አሳስባለሁ።
ልዑል እግዚአብሔር አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ያስታግሥልን!
©️ ስምዓኮነ መልአከ / Simakone Melak
