በአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛው የመንገድ ዳር አደጋዎች የሚከሰቱት፤ በተጨናነቁ መንገዶች ላይ ሳይሆን ለአሽከርካሪዎች ምቹ ተደርገው በተሰሩ ክፍት መንገዶች ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአሐዱ አስታውቋል።
የዚህም መንስኤ የአሽከርካሪዎች ባህሪ እና በፍጥነት በማሸከርከር መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የፍጥነት ቦታዎች ታሳቢ ባለማድረግና እይታን በሚጋርዱ ወይንም ‘እግረኛ ይበዛበታል’ ብሎ ባለማሰብ አሽከርካሪዎች በፍጥነት ስለሚያሽከርሩ፤ አብዛኛው የትራፊክ አደጋ በመዲናዋ ምቹ እና ክፍት በሆኑ መንገዶች ላይ እንደሚከሰት በኮሚሽኑ የትራፊክ አደጋ ምርመራ የግድያና አደጋዎች መርማሪ ኢንስፔክተር ተመስገን ደሳለኝ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ኢንስፔክተር ተመስገን አክለውም፤ ለእግረኛ ቅድሚያ በማይሰጡ፣ አልኮሎች ጠጥተው በሚያሽከረክሩና ከመጠን በላይ በፍጥነት በሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች አደጋዎቹ እንደሚደርሱ ጠቁመዋል።
ይህም በመሆኑ ችግሩ በሰው፤ በንብረት ላይ እንደ ሀገር ትልቅ ኪሳራ እያደረሰ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ኢንስፔክተሩ አያይዘውም በአጠቃላይ ከደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ውስጥ፤ በቦሌ ክ/ከተማ 22፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ደግሞ 20 የመንገድ ዳር አደጋዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ከሌሎች የትራፊክ መጨናነቅ ካሉባቸው አከባቢዎች አንጻር፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለምዶ መርካቶ አካባቢ 4 አደጋዎች መከሰታቸውም ገልጸዋል።
“ይህም አብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ የሚደርሱ አደጋዎች የትራፊክ መጨናነቅ ወይንም የሰዎች ፍሰት በሚበዛበት ሳይሆን፤ በዋናነት ለአሸከርካሪዎችና ለእግረኛ ምቹ ተደርገው በተሰሩና ክፍት በሆኑ መንገዶች ላይ እንደሚከሰቱ ማሳያ ነው” ብለዋል።
በአጠቃላይም፤ 138 የትራፊክ አደጋዎች ተከስተው፣ 151 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የገለጹት ኢንስፔክተር ተመስገን፤ ከእነሱም ውስጥ 103 ወንዶች ሲሆኑ 48 ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ከ5 ዓመት በታች ያሉ 6 ሕጻናት በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የገለጹ ሲሆን፤ “55 የሚሆኑት ዜጎች ደግሞ ከ35 ዓመት እድሜ ክልል በታች ያሉ አምራች ዜጎች ናቸው” ብለዋል፡፡
ቁጥራዊ መረጃዎቹ ከሐምሌ 1 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ብቻ የተከሰቱ እንደሆነ አስታውሰው፤ ይህንን እንደምሳሌ ያነሱት አብዛኛው የትራፊክ አደጋዎች ምቹ መንገዶች እንደሚከሱቱ ለማሳወቅ እንደሆነም ነግረውናል።
“አሽከርካሪዎች የትራፊክ ሕጉን አክብረው በማሽከርከር የራሳቸውን እና የሌሎችን ሕይወት ከመቅጠፍ እንዲሁም ንብረት ከማውደም እንዲጠበቁ፤ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው” ብለዋል።
“አሽከርካሪ ይጠብቀኛል” ብለው ሳይጠነቀቁ በመኪና መንገድ ላይ የሚሄዱ እና የሚያቋርጡ፣ ቆመው የሚያወሩ፣ የሚጫወቱ እግረኞችም መኖራቸውን ጠቁመው፤ ድርጊቱ መታረም እንዳለበት አሳስበዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
