አንጋፋው አርቲስት መርዓዊ ስጦት ከዚህ አለም ድካም አረፉ
የወርቃማው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ባለውለታ አርቲስት መርዓዊ ስጦት በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደም ቦታ ከሚይዙ አንጋፋ ሙዚቀኞች መካከል አንዱ ናቸው ።
ከሀምሳ አምስት ዓመት በላይ በቆየበት የሙዚቃ ህይወቱ በክላርኔትና አልቶ ሳክስ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት በሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲነት በአቀናባሪነት እንዲሁም በኃላፊነት (አመራር) ቦታ ላይ ለበርካታ አመታት አገልግለዋል ።
የአምባሰሉ ንጉስ የክላርኔት ንጉስ በመባል የሚታወቀው ጋሽ መርዓዊ ስጦት ውልደትና እድገታቸው ከወሎ አምባሰል ልዩ ስሙ ዳቃ ወረዳ ነው ። ከአምባሰል ወጥተው በክላርኔት አምባሰልን ወደር በማይገኝለት ሁኔታ በመጫወት በሙዚቃ መድረክ ላይ ነግሰው ኖረዋል ። አርቲስት መርዓዊ ስጦት አምባሰልን ሲጫወቱ አይቶ ስሜቱ የማይኮረኮር ፣ የማያነባ የለም ።
የሙዚቃ ህይወታቸው የሚጀምረው በ1942 ዓ.ም ገና የ14 አመት ልጅ እያሉ የማዘጋጃ ቤት በወቅቱ የሙዚቃ እና ቴአትር ማስፋፊያ “ጎንደሬው ገብረማርያም ” የተሰኘ ቴአትርና የመንገድ ላይ የሙዚቃ ትርኢት (ፋንፋር ባንድ) ለማሳየት ደሴ በመጡበት ወቅት ልባቸው ይሰረቅና እሳቸውም እንደነሱ መሆን እንደሚፈልጉ በመጠየቃቸው አዲስ አበባ ከመጡ እናስተምሮታለን ይሎቸዋል።
ይህ ቃል በጊዜው ከሰጡት ውስጥ አንዱ ተስፋዬ ሳህሉ “አባባ ተስፋዬ ” ነበሩ ። እሳቸውም ለአዲስ አመት የእንቁጣጣሽ አበባ ስለው በየሹማምንቱ ቤት በማዞር ሀምሳ ብር ይሰበስቡና ወዴት ነህ የሚለው ጥያቄ እንዳያስጨንቃቸው ሆን ብለው ብርድ ልብስ ቀደው ላሰፋ ነው ። በሚል ሰበብ ከቤት ይወጣኑ ከአንድ ጣልያናዊ ሹፌር ጋር ተነጋግረው በትሬንታ ኳትሮል ተጭነው ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ ።
አጠያይቀውም ቃል የገቡላቸውን ሰዎች ያገኙና በአስራ አራት አመታቸው የሙዚቃ ትምህርታቸውን ይጀምራል ። ከትምህርታቸው ጋር አንድ ላይ ማደርያና የኪስ ገንዘብ ጭምር ይሰጣቸው ነበር ። በወቅቱ ከእሳቸው ጋር አብረው ከነበሩት ሙዚቀኞች መሀል የሳክስፎኑ ንጉሥ ጌታቸው መኩሪያ አንዱ ናቸው ። ስድስት አመት በዚህ ሁኔታ ካሳለፉ በኋላ የጃንሆይ 25ኛ የብር ኢዩቤልዩ በአል ምክንያት በማደረግ የአሁኑ ብሄራዊ ቴአትር የቀድሞ ቀ. ኃ.ስ ቴአትር ቤት ሲቁቋም ከተመረጡት አስራ ሶስት ሙዚቀኞች መካከል አንዱ በመሆን መስራች ሆኑ ።
በአርመናዊው አስተማሪና አለቃቸው ሙሴ ነርሲስ በምግባራቸውም ሆነ በትምህርት አቀባበላቸው የሚደነቁት አርቲስት መርዓዊ ከሙሴ ነርሲስ ህልፈት በኋላ የሙዚቃ ክፍሉን ተረክበው ለሰላሳ አመታት በአለቃነት አገልግለዋል። በዚህም ወቅት ለአርቲስት ምኒልክ ወስናቸው ፣ ለመልካሙ ተበጀ ፣ ጠለላ ከበደ ፣ ፍቅርተ ደሳለኝ . . . ለበርካቶች ግጥምና ዜማ ደርሰዋል ። ሙዚቃ አቀናብረዋል ። ከነዚህም ውስጥ የምኒልክ ወስናቸው የእንጆሪ ፍሬ፣ ትዝታ አያረጅም፣ስኳር ስኳር፣ አፈር አትንፈጊኝ፣ በምድረ ሱዳን ያለሽው ፣ ጥቁሯ ጽጌረዳ፣ የመልካሙ ተበጀ፣ ብእር ብእር ፣ ሰላም ጤና ይስጥልኝ፣ ንቢቱ፣ የፍቅርተ ደሳለኝ ልማት ልማት ሌሎችም ይገኙበታል ።
ከዚህም ባሻገር ከ200 የማያንሱ አብዮታዊ መዝሙሮችን፣ ለሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን እና ለሌሎችም በርካታ ታዋቂ ቴአትሮች ማጀቢያ ሙዚቃዎችን ደርሰዋል ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብም የመጀመርያ የሆነውን የክለቡን መዝሙር የሰሩት አርቲስት መርዓዊ ስጦት ናቸው ። በአፄ ኃይለስላሴ ፣ በዘመነ ደርግ እና በዘመነ ኢህዲግ ጊዜ በተሰራው የኢትይጵያ ህዝብ መዝሙር ላይ የጋሽ መርዓዊ ትንፋሽ ተቀርጿል! ዜማው በሚሰራበት ጊዜም ኦርኬስትራውን የመምራትና የማስተባበር ስራውን የሰረት ጋሽ መራዊ ስጦት ናቸው ።
በሙያው All Black People Music Festival ጨምሮ በናይጄሪያ ፣ በግብጽ በሱዳን ፣ በቻይና በራሺያ ፣ በአሜሪካ እና ሌሎችም ሀገራት ሀገሩን ወክሎ ተሳትፈዋል ። በአሜሪካ ሀገርም ከሙዚቀኛ ያሬድ ተፈራ ጋር በመሆን አምባሰልና ትዝታ ለትውልድ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲተላለፍ በካሴትና በሲዲ አስቀረጸዋል ። ለዚህና መሰል አስተዋጽኦ በተለያዩ ጊዜያት ሽልማትን አግኝተዋል ።
★ ከጃንሆይ የማበረታቻና የመጻህፍት ሽልማት
★ በደርግ ጊዜ በማስታውቂያ ሚኒስትር የምስጉን ሰራተኛ ወርቅ ተሸላሚ።
★ የአለም አቀፍ ጎልድ ሜርኩሪ ሽልማት (ሽልማቱ አለማቀፋዊና ትላልቅ የአለም መሪዎችን ጨምሮ ሳይንቲስቶችና ምሁራን የሚሸለሙት ነው )
★ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር የወርቅ ሽልማት
★ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ማህበር የክብር ሽልማት ።
★ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር (ባህል ማዕከል) የክብር ዋንጫ ተሸላሚ።
★ ከጠ/ሚ አብይ አህመድ የክብር ሜዳሊያ ሽልማት ጥቆቶቹ ናቸው።
ጋሽ መርዓዊ ጡረታም ከወጡም በኋላ ከሙዚቃው ሳይርቁ እስከ ቅርብ ጊዜ ከብሄራዊ ቴአትር ደጅ አይጠፋም ። የልብ ህመም አጋጥሞቸው የትንፋሽ መሳሪያ መጫወት እስከተከለከሉበት ጊዜ ድረስ ክላርኔታቸውን ይዞው መገኘት ባለባቸው ቦታ ሁሉ እየተገኙ ህዝብን ያስደስቱ ነበር ። በህይወታቸው ከኦርኬስትራው ተነጥለው በየትኛውም ምሽት ክለብ ሰርተው አያውቁም ። በተሰጥኦ ያምናሉ ። አዳዲስ ወጣቶች በመጡም ጊዜ ካሉበት አድኖ በማግኘት እና በማበረታታት ይታወቃሉ።
አርቲስት መርዓዊ ስጦት ባላቸው ጊዜ ሁሉ ባለተሰጦ ልጆች በማደን ችሎታቸውን እያደነቁ ፣ እየመከሩ የሚያበረታቱና ምን አይነት አርቲስት መሆን እንዳለባቸው ምሳሌ በመሆን ጭምር የሚደግፍ የሙያ አባትም ጭምር ናቸው ! ለዚህም “የአለም አቀፍ ሜርኩሪ” ሽልማታቸው ወጣት ባለሙያዎች ባዩት ጊዜ እንዲበረታቱበትና እንዱነሳሱበት በማሰብ በስጦታ መልክ ” ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ዋና ስራ አስኪያጅ ቢሮ እንዲቀመጥ አስረክበዋል ።
