ጥቅምት 28 እና 29 እ.ኤ.አ.3ኛው የሩሲያ – አፍሪካ ጉባኤ በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በታላቁ ክሬምሊን ቤተ-መንግሥት ይካሄዳል።
ይህ ታሪካዊ ጉባኤ በሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ቪላዲሚር ፑቲን እና የአፍሪካ ህብረት ወቅታዊ ሊቀመንበር የሆኑት የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኤቫሪስት ኑዳይሺሚዬ በጋራ ሰብሳቢነት ይመራል።
በዚህ ስብሰባ ላይ ከአህጉሪቱ 54 ሀገራት መካከል የ48ቱ ሀገራት ልኡካን ቡድኖች መገኘታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፣ 22ቱ ሀገራት በቀጥታ በፕሬዝዳንቶቻቸው እና በመንግሥት መሪዎቻቸው ደረጃ ይወከላሉ።
ይህም እ.ኤ.አ. በ2023 በሴንት ፒተርስበርግ ከተካሄደው 2ኛው ጉባኤ የ17 ሀገራት መሪዎች ተሳትፎ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ ያለው ነው።
ቀሪዎቹ ሀገራት በምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትሮች እና አምባሳደሮች የሚወከሉ ሲሆን፣ እንደ የአፍሪካ ህብረት፣ AfCFTA፣ EAC፣ IGAD፣ COMESA፣ SADC እና Afreximbank ያሉ በርካታ አህጉራዊ የኢኮኖሚ እና ቀጠናዊ ውህደት ተቋማት መሪዎችም ይሳተፋሉ።
በስብሰባው ላይ ከተገገኙ ታዋቂ መሪዎች መካከል የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ፣ የአልጄሪያው ጠ/ሚ ሲፊ ግሪብ፣ የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ፣ የኡጋንዳዋ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሲካ አሉፖ ፣ የማሊ ፕሬዚዳንት አሲሚ ጎይታ፣ የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒው ፕሬዚዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ ምባሶጎ እንዲሁም የኤርትራውን ፕሬዝዳነት ጨምሮ ሞስኮ ገብተዋል።
በተጨማሪም እንደ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ሞሪታኒያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ቶጎ፣ ፣ ሶማሊያ እና ኮሞሮስ ያሉ ሀገራት ከፍተኛ የልኡካን ቡድኖቻቸውን ልከዋል
የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳ በሩሲያ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ዘሁለገብ ግንኙነት ማለትም በፖለቲካ፣ በንግድና ኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በሰብአዊና ባህላዊ ዘርፎች ማጠናከር ነው።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የጉባኤው የመጨረሻ ዲክላሬሽን፣ ከ2027 እስከ 2029 የሚዘልቅ የድርጊት መርሃ-ግብር፣ እና ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የሰው ሰራሽ አስተዋጽኦ (AI) ቴክኖሎጂ ትብብር ዲክላሬሽን ይጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ በርካታ አህጉራዊ ስምምነቶችም ይፈረማሉ።
በመጀመሪያው ቀን ጥቅምት 28፣ ፕሬዝዳንት ቪላዲሚር ፑቲን እና ፕሬዝዳንት ኤቫሪስት ኑዳይሺሚዬ የሁለቱም ወገኖች የመንግስት አካላት፣ የንግድና የኤክስፐርት ቡድኖች በሚሳተፉበት የሩሲያ – አፍሪካ ኢኮኖሚክ እና ሰብአዊ ፎረም ላይ ንግግር ያደርጋሉ።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ፑቲን ከቀጠናዊ ድርጅቶች መሪዎች ጋር የሚመክሩ ሲሆን፣ በጉባኤው ጎን ለጎንም ከአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር ተከታታይ የሁለትዮሽ ውይይቶችን እንደሚካሄዱ የአፍሪካ ኒውስ እና የስፑትኒክ አፍሪካ ዘገባ ያመላክታል።
