በኢትዮጵያ ከ1.6 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕብረተሰብ ከፍተኛ የእይታ ችግር ያለበት ሲሆን፣ 3.7 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የእይታ እክል እንዳለበት ተገለጸ።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን እንደገለጹት፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ በትራኮማ የሚከሰት የእይታ ችግር፣ ግላኮማ እንዲሁም ከዕድሜ እና ከማኅበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙ ችግሮች ለሀገሪቱ የዓይን ጤና ዋነኛ ፈተናዎች ናቸው።
ዶክተር ሕይወት አክለውም የዓይን ጤና ችግርን በዘላቂነት ለመቀነስ የሚያስችል እና በቅርቡ የሚጀመር ወደ 300 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ የሚጠይቅ ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የዓይን ዳሰሳ ጥናት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
እንደ መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለጻ፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ችግርን ለመቅረፍ በየዓመቱ ለ75 ሺህ ዜጎች ይሰጥ የነበረውን የሕክምና አገልግሎት ባለፈው ዓመት ከ123 ሺህ በላይ ማድረስ ተችሏል።
በተጨማሪም በዓመቱ ከ87 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ነፃ የትራኮማ ሕክምና አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ 2025 ባሉት ዓመታት ደግሞ ከ377 ሺህ በላይ የዓይን ቆብ መታጠፍ ችግር ያለባቸው ዜጎች በቀዶ ሕክምና መታከም ችለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 2.2 ቢሊዮን ገደማ ሰዎች ከእይታ ችግር ጋር የሚኖሩ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል አብዛኞቹ መከላከል ወይም መታከም የሚችሉ ናቸው።
በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት የዓይን ሕክምና አገልግሎት ከሚፈልጉ ሰዎች መካከል እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት እንደሚያጡ የተገለጠ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ከፍተኛ የዓይን ችግር ካለባቸው ሀገራት ተመዳጅ መሆኗ ተጠቅሷል።
በመጨረሻም የዓይን ጤና ሁኔታ ሳይወሳሰብ እና የእይታ ማጣት አደጋ ሳይከሰት ቅድመ-ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑ ተነስቷል።
