ብቻዬን ቆሜያለሁ

Date:

(I stand alone)

ያዕቆብ ብርሃኑ

ጥሎብኝ የFM ሬዲዮኖቻችን ማዳመጥ አልወድም። ከመጻሕፍት ውጪ ቴሌቪዥን እንኳን በቤቴ የለኝም፡፡ የሆነ ዕለት ድንገት፣ ድንገት እንደዘበት የሸገር ሬዲዮ ስልኬ ላይ ስከፍት መዓዛ ብሩ ኘሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴን “ሠው አልተረዳኝም ብለው ያስባሉ? ለምንስ አልተረዱኝም ብለው ተጨንቀው ያውቃሉ?” የሚል መንፈስ ያለው ጥያቄ ስትጠይቃቸው ሠማሁ። መልሳቸው መስጦኛል።

“እንኳን ሌላው ሠው ልጄም ላይረዳኝ ይችላል። የጋራ በሆኑት የሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ እየተነጋገሩ መኖር ነው። ለምን አልተረዱኝም ብዬ አልጨነቅም። እንዲረዱኝም አልጠብቅም። ከታላላቆቹ ከእነ ሶቅራጥስ ብትጀምሪ የትኛው ሠው ተረድቷቸዋል?” መልሳቸው ነበር።

እውነት እኮ ነው። በየመስሪያ ቤቱ፣ በየግንኙነት መድረኩ ጥቂት ከመንጋው ነጠል በማለታቸው እንደ ጉዱ ካሣ ‘ጉዱ እንትና’ እየተባሉ የተገለሉትን ቤቱ፣ ደጁ ይቁጠራቸው። ከመንጋው መስመር ነጠል ያሉትን ማግለል የኢትዮጵያዊያን ብቻ ክፉ ውርስ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ግን ምዕራባዊያኑ ይህን ለመሠሉ ሠዎች መስተናገጃ የበዛ ሆደ ሰፊነት ሳይኖራቸው ይቀራል? ለዚህ ይሆን ዛሬ ዓለምን ከጫፍ ጫፍ ያጥለቀለቀውን ሥልጣኔ መገንባት የቻሉት?

እኔ እንኳን እንደ አቅሚቲ ገና ከጅምሩ የዚህ ገፈት ቀማሽ ሆኛለሁ። በሕይወት አጋጣሚ በሕይወት መበርገጌን ብቻ ታቅፌ እንደ አምባሣደር ብርሃኑ ድንቄ ‹‹ብቻዬን ቆሜያለሁ! I stand alone›› ማለት ከጅሎኛል። አምባሳደር ብርሃኑ የንገሱን አገዛዝ ተቃውመው ራሳቸውን ከማግለላቸው በፊት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ፡፡ አጀባቸው እልፍ ነው፡፡ ወዳጆቻው እንኳን ዲፕሎማቶች፣ የሀገራት መሪዎች፣ ታላላቅ ሰባኪያን፣ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ ራሳቸውን ካገለሉ ጀምሮ ግን ሁሉም ለንጉሱ ቀና አስተሳሰብ በነበረው በአሜሪካ መንገስት መጠቆርን ሽሽት ገለል አደረጓቸው፡፡ አምባሣደሩም ከንጉሡ ጋር በፈጠሩት ውርክብ በዙሪያቸው የነበሩት ሰዎች ሲሸሹ ተገቢ ያልሆነ ብቸኝነትን የመፍራት ድንጋጤ ውስጥ ተዘፈቁ፡፡ I Stand alone በተሰኘች ሚጢጢ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ…

‹‹ለእኔ ጓደኛ ማለት ጓደኛ ነው፡፡ ያሉኝን ጓደኞች ማጣት ወይም አዲስ ጓደኛ ማፍራት አልፈልግም፡፡ አንዳንዴ ምነው ለጓደኝት ደንታ ባልሰጠኝ እላለሁ፡፡ ሆኖም ግን በብቸኝነት ለመኖር እየጣርኩ እንኳን ያለጓደኛ መኖር አልሆነልኝም።

አንድ ጊዜ የዋሽንግተንን መጥፎ ስሜት ለማምለጥ ወደ ኒውዮርክ ከተማ ሄድኩ፡፡ እዚያም አንድ ሆቴል ገባሁ፡፡ ብቸኝነት በጣም ስለተሰማኝ ካኘሁት ሰው ጋር በማንኛውም አርዕስት ላይ መነጋገር ፈለኩ፡፡ ግን ከማን ጋር አወራለሁ? ሆቴል ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ዞር ብሎ እንኳን ያየኝ ሰው አልነበረም፡፡ ወዲያው ከሆቴል ወጥቼ ወደ ባቡር ጣቢያ አመራሁ፡፡ በዚያ ሠዓት ሰዎች ከስራ ወደ ቤት ለመመለስ ይጣደፉ ነበር፡፡ እኔም ከሰው ጋር ተቀላቅዬ ቶሎ ቶሎ መራመድ ጀመርኩ፡፡ ወደ የት እንደሚሄድ ሳላውቅ በጣም የተጠቀጠቀ አንድ ባቡር ውስጥ ገባሁ፡፡ ሰው እርስ በእርሱ ይጋፋል፤ ይተያያል፤ ቃል የሚተነፍስ አንድም ሰው ግን አልነበረም፡፡

ከሰው ጋር መቀላቀሌ ለጊዜው ደስታ ሰጠኝ፡፡ ባቡሩ ውስጥ ያሉት ሰዎች ማየት እንጂ መናገርና መስማት የማይችሉ መስለው ታዩኝ፡፡ ስንተያይ ‹እወድሃለሁ፤ እወድሻለሁ፤ እጠላሻለሁ፤ እጠላሃለሁ ወይም የራስሽ፣ የራስህ ጉዳይ› የሚል ስሜት በገጻቸው የሚነበብ ይመስላል፡፡ ይህም ግንኙነት ነው፡፡ ለጊዜው ብቸኝነቴን አስረስቶኛል፡፡››

የእኔ የጓደኝት ግንዛቤ ግን ከአምባሳደሩ የሚለይ መሰለኝ፡፡ ጓደኝነት ለእኔ ሌላ፣ ፍጹም ሌላ ጣዕም ያለው ዘና ብሎ ጨረቃን የመጎብኘት ያህል አቅልን የሚያስት መደመም፣ መደነቅ የታከለበት ጀብዳዊ ጥምረት ነው፡፡ እንጂ እንዲያው እንደ አሳሞች እየተጋፉ፣ በየካፌው፣ በየምግቤቱ እየተገናኙ ድድ የማስጣት ሂደት አይደለም፡፡ ጓደኝነት የነፍስን ያህል ረቂቅ ነው፡፡ ይወለዳል፤ ሊያድግ ይችላል፤ ሂደቱን ሲጨርስ ድብን ብሎ ይሞታል፡፡ ጉድኝቱ የላቀ፣ የረቀቀ፣ በየዕለቱ የሚታደስ ሌላ ለዛ ያለው መስተጋብር እስከሌለው ድረስ የማውቀው ሰው ሁሉ ጓደኛዬ አይሆንም፡፡ የሚያውቁትን ሰው ሁሉ ወዳጅ ጓደኛ ለማድረግ የሚማስኑ ሰዎችን ሳይ አዝንላቸዋለሁ፡፡ ይህች ስንዝር ሕይወት እንኳን ለግብስብስ መንጋ ለጽሞናም የሚበቃ ተራፊ ጊዜ የላት፡፡

እኔ ግን ከአምባሳደር ብርሃኑ እለያለሁ፡፡ እንዲያው መሸሹ ተመችቶኛል። ምክንያቱም የሆነን ሰው ወደ ሕይወትህ ባስገባህ ቁጥር ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ አደገኛ ፈንጂ ራስህ ላይ እየጠመድክ መሆኑን አትርሳ፡፡ ለምን? እያንዳንዱ ወዳጅነት በነገ ውስጥ ሊገለጥ የሚችል የጠላትነት ዘር በውስጡ አዝሏልና፡፡

አዎ እኔ ከአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ሳልለይ አልቀርም፡፡ ምንም ነገር፣ ጠብ እንኳን ቢሆን ሚስቲክ የሆነ፣ የተሻገረ፣ ከቶውንም በሌሎች ያልታሰበ ሌላ ጣዕም እንዲኖረው እፈልጋለሁ፡፡ የምንኖረው ግን በጅምላ በሚመለክበት፣ በጅምላ በሚወገዝበት፣ በጅምላ በሚኮነንበት፣ ሽያጩም፣ ዘረፋውም፣ ግድያውም፣ ቀብሩም ሁሉ ጅምላ ሆኖ ተነጥሎ መቆም ወንጀል በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ እናስ በዚህ ሂደት ከመንጋው የመነጠል፣ ከዘመን የመጣላት፣ ከትውልድ የመኳረፍ አዝማሚያ የሌለው ጠቢብ ረብ ያለው ሀቲት ሊወጣው ይችላልን? የመንጋውን መፈክር በውብ ቃላት ሸላልሞ ከማተም በስተቀር… በሠዎች መካከል ስትሆን ደቃቅ አሸዋ ላይ እንደወደቀች አንዲት የጤፍ ዘር ታንሣለህ፡፡ ምርጫህ በሌሎች ምርጫ ይወሰናል፡፡ ድምጽህ በሌሎች ጩኸት ይሸፈናል፡፡ ቁጣህ በሌሎች ግድየለሾች ፌዝ ይከለላል፡፡ ሕማም፣ ሕመምህ በሌሎች ለዛየለሾች ሁካታ ይጨፈለቃል… 

የተሣሣተው አስተሣሠባችን እንጂ ሠውን ትንሹ እግዜር ያደረገው ሠው እኮ ድንጉጥ፣ ደካማ፣ አሣዛኝ፣ ፈሪ ፍጥረት ነው። ሠው ስለዓለም ካለው ዕውቀት ሁሉ ትንሹ ስለ ራሱ ያለው ዕውቀት መሆኑ አይገርማችሁም? ማን እንደነገገው የማናውቀው ግን ዙሪያችን የከበበን ክልከላ አበዛዙ ለጉድ ነው፡፡ ማን እንደከለከለው የማይታወቅ ‹ክልክል ነው!› እኛ ጋ አበዛዙ ትንግት ያሰኛል፡፡ ማቀፋችንን እንጂ ምን፣ ለምን እንዳቀፍን ግድ አይሰጠንም፡፡ ነገረሥራችን ሁሉ በነሲብ የሚከናወን ነው፡፡… እናም ተጠየቅ በሌለበት በልማዳዊ አስተሳሰብ የተቃኘ ማኅበረሠብ መካከል እየኖራችሁ እንደ ትንኝ የሚዋነቡ ጥቂት ጥያቄዎች ካሏችሁ ሠው አልተረዳኝም ብላችሁ አትጨነቁ፡፡ ዛሬ ለስሙ እንሰዋለን የሚሉ ቢሊዮናት ተከታዮች ያሉት ኢየሱስ እንኳን በዚያች ዕለት፣ በመጨረሻዋ ሠዓት ይህ ዕጣ ገጥሞት ከመስቀሉ ፊት ለፊት ለብቻው፣ ለብቻው!  ነበረ፡፡ (አስተያየቶን singofbird@gmail.com ላይ ሊያደርሷቸው ይችላሉ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...

ትራምፕ ኢራን ላይ ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር...