በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት የክረምት ወቅትነቱን ተከትሎ የወባ ወረርሽኝ በስፋት ሊከሰት እንደሚችል ይገመታል፡፡
የወባ በሽታ በትንኝ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በዋነኛነት በትኩሳት የሚገለጥ ተወሳስቦ ለከፍተኛ አደጋ ሊዳርግ የሚችል በሽታ ነው፡፡
የወባ በሽታ በዓለም ላይ የበርካቶችን ህይወት የሚቀጥፍ በትንኝ አማካኝትት የሚከሰት ተላላፊ በሽታ እንደሆነም ይነገራል፡፡
የወባ በሽታ ሲታሰብ ትንኟ ከታማሚ ሰው የበሽታውን ተህዋስ በተለይ በኢትዮጵያ ፕላዝሞዴም ፋሲፋረም በተለምዶ ቢጫ ወባ የሚባለውን እና አንድ ሶስተኛው ደግሞ ቫይቫክስ በተባለ ተህዋስ ዝርያ የሚከሰት ነው፤ ወባዋ የበሽታውን ተህዋስ ከታመመ ሰው አሊያም ታሞ ከዳነ ሰው ትወስዳለች፡፡
ወንድ እና ሴቴ ተህዋስ በወባ ውስጥ አንድ ሳምንት ያድግና ትንኟ ለመራባት የሰው ደም የሚያስፈልጋት በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ሰውን በምትነክስበት ጊዜ በሽታውን ወደ ሌላ ሰው ታስተላልፋለች፡፡
ትንኟ ለመራባት ቆላማ አካባቢ በመምረጥ ከባህር ጠለል በላይ 1ሺህ 400 ሜትር በታች በሆኑ አካባቢዎች ላይ እንደምትገኝና ከዛ በላይ ባለ ከፍታ የመራባት ምጣኔዋ እንደሚቀንስ ይገለፃል፡፡
በሽታው ከዚህ በፊት ለተያዘ ሰው እንዲሁም በተለይ ነብሰ ጡር እና ህፃናት ላይ የመከላከል አቅማቸው አናሳ በመሆኑ የከፋ ጉዳት ያደርሳል፡፡
በአብዛኛው የክረምት ወቅት አልፎ የበጋ ወቅት ሲጀምር ውሀዎች ሙሉ ለሙሉ ስለማይደርቁ እና የታቆሩ ውሀዎች ስለሚኖሩ እንዲሁም በትንንሽም ውሀዎች የመራባት እድል ስለሚኖር ለትንኞች መራባት አመቺ ይሆናል፡፡
የወባ በሽታ ምልክቶች፦
- ትኩሳት • ቁርጥማት • ማስመለስ • ማስቀመጥ
- ብርድ ብርድ ማለት • የከፋ ሲሆን ደግሞ አይን ቢጫ ያደርጋል፡፡
የወባን በሽታን ለመከላከል ትንኟ የምትራባባቸውን ቦታዎች ማጽዳት ያስፈልጋል ያቆሩ የቆሸሹ ነገሮችን ማስወገድም ይገባል፡፡
ጸረ-ትንኝ ኬሚካሎች በሚረጩበት ጊዜ ቀለም መቀባት፣ ማጠብ እንደማይገባ እንዲሁም በጸረ ትንኝ የተነከረ አጎበር መጠቀም እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
