የኡጋንዳው ፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የአባይን ጉዳይ “ታሪካዊ መብት” ከሚል እይታ ተላቆ የሁሉንም ተፋሰስ ሀገራት ፍላጎት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ልናየው ይገባል አሉ፡፡
ፕሬዘዳንት ሙሴቪኒ ይህንን በኤክስ ገፃቸው ላይ የፃፉት ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በካይሮ ተገናኝተው ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡
ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በውይይታቸው ወቅት ስለ አባይ ወንዝ የወደፊት ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ሙሴቪኒ ጠቅሰዋል፡፡
የአባይን ጉዳይ ሰፋ ባለ እይታ መመልከት አለብን ያሉት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት አንዳንድ ጊዜ ችግሮች የሚያጋጥሙት ለጉዳዩ ባለን አቀራረብ ነው ብለዋል፡፡
“ታሪካዊ መብቶች” ላይ ከማተኮር ይልቅ የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች አለም አቀፍ ፍላጎትን ማጤን አለብን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ግባችን ሊሆን የሚገባው ብልፅግና ለሁሉም ፣ የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነት ለሁሉም፣ መስኖ መጠቀም ለሁሉም፣ ለሁሉም ንፁህ የመጠጥ ውሃ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህን አላማዎች በማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት ሳይንሳዊና ፍትሃዊ ዘዴዎችን ተጠቅመን ተግባራዊ ልናደርገው እንችላለን ሲሉ ዩዌሪ ሙሴቪኒ በኤክስ ገፃቸው ላይ ፅፈዋል፡፡
