አጠቃላዩ የኮሪደር ልማት አሠራር ለመጪው ጊዜ ታላቅ ተስፋ የሚሰጠን ነው። በመጀመሪያው ምዕራፍ በአራት ኮሪደሮች ጀምረን በሁለተኛው ምዕራፍ በስምንት ኮሪደሮች ቀጥለናል።
የተጠናቀቀውንና 12 ነጥብ 74 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ከአዲስ ኮንቬንሽን መዐከል-ጎሮ-ቪአይፒ ኤርፖርት ኮሪደር ዛሬ ተመልክተናል።
በኮሪደሩ 29 ኪሎሜትር የእግረኛ መንገድና 15 ነጥብ 27 ኪሎሜትር የብስክሌት መጋለቢያ ተሰርቷል።
ይኽ የኮሪደር ሥራ ሰፋፊ የተሽከርካሪ መንገዶችን፣ ከጎሮ እስከ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ መንገድ እንዲሁም በአካባቢው ሰፊ የወንዝ ልማትን ያካተተ ነው። ሰባት የስፖርት ማዕከላት፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የታክሲና አውቶቡስ መናኸሪያዎች፣ ካፌዎች፣ የሕዝብ መጸዳጃዎችና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች የተካተቱበት ነው። እነኚህ ግንባታዎች ሥራ ፈጥረዋል፣ መገናኛ እና መዳረሻዎችን አስፋፍተዋል፣ የከተማዋን መሠረተ ልማት አጠናክረዋል።
በሁሉም መስክ ኢትዮጵያ መበርታቷን ቀጥላለች። ወደ ብልጽግና የምናደርገው ጉዞ አይደናቀፍም። አይቆምም። የእነኚህ ሥራዎች ስኬት ይኽንን ያስቻለውን የተለወጠ ርዕይና የሥራ ባሕል ያንፀባርቃል።
እስከአሁን የከተማዋ ግማሽ ያህል የተለወጠ ሲሆን የበለጠ ለማሻሻል የምንተጋባቸው ከባቢዎች አሁንም ይቀራሉ።
