በዓለማችን ላይ ቡና ላይ እሴት ጨምረው ቆልተው፣ ፈጭተውና አሽገው ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ፣ ቡና የማያበቅሉ ሀገራት አሉ ቢባል ነገሩ ያስገርማል።
እንዴት? ካሉ ከሌሎች አምራች ሀገራት ቡናን በማስገባትና እሴት በመጨመር ነው መልሱ።
በዚህም መሰረት በጀርመን የተለያዩ ከተሞች ከ500 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የቡና ማቀነባበሪያ ድርጅቶች ይገኛሉ። እነዚህ የቡና ማቀነባበሪያ ኩባንያዎች ከብራዚል፣ ቪዬትናምና ከሌሎች ሀገራት ጥሬ ቡናን በማስመጣትና በማቀነባበር መልሰው ወደ ውጪ ሀገራት ይልካሉ። በዚህም በየዓመቱ በቢሊየን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ እያገኙም ነው።
ቡናን ቆልቶ በመፍጨትና አሽጎ በብዛት ለገበያ በማቅረብ ከዓለም በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ከምትገኘው ጀርመን በመቀጠል ሁለተኛና ሶስተኛ የሆኑት ደግሞ ስዊዘርላንድና ጣልያን ናቸው።
እነዚህም ሀገራት በተመሳሳይ ቡናን ለማብቀል የሚያስችል የአየር ንብረት ባይኖራቸውም፣ ጥሬ ቡና አምራች ከሆኑ አገራት ይልቅ የቡና ኢንዱስትሪዎች በብዛት ስላላቸው ትርፋማ ናቸው።
ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያና ሌሎች ቡናን በስፋት ለሚያመርቱ ሀገራት አንድ መልዕክት ያስተላልፋል። ይኸውም ቡናን ከማምረት ባለፈ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ አዋጭ መሆኑን ነው፡፡
ቡናን በማቀነባበርና በተለያየ የቡና ውጤቶች ላይ በማተኮር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል የአውሮፓውያኑ ሀገራት ተሞክሮ በቂ ማስረጃም ነው።
Via ebc-
