ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችላቸውን ስትራቴጂካዊ የአጋርነት ትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ።
“ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ” በሚል ስያሜ የተፈረመውን የትብብር ስምምነት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማሳደግ በአውሮፓውኣን 2016 ለተፈረመው የስትራቴጂያዊ ትብብር ስምምነት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑም ተመላክቷል።
ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ እና በአውሮፓ ኅብረት በኩል የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን ፈርመዋል።
የትብብር ስምምነቱ በዲጂታላይዜሽን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በምግብ ሥርዓት፣ በጤና በመሰረተ ልማት እንዲሁም በሰላምና ጸጥታ ሁለቱ ወገኖች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት “ግሎባል ጌትዌይ” በኢትዮጵያ እና በኅብረቱ መካከል የጋራ ስትራቴጂያዊ ራዕይ ለመቅረፅና አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር በትክክለኛው ወቅት ይፋ መደረጉን ፕሬዚዳንት ታዬ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ላለው የረጅም ጊዜ አጋርነት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑንም ፕሬዚዳንት ታዬ እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በጋራ በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።
(#አዲስ_ማለዳ)
