በአሜሪካ ኬንታኪ ግዛት ትናንት ምሽት በደረሰ የዩፒኤስ ጭነት አውሮፕላን መከስከስ አደጋ የ7 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
የጭነት አውሮፕላኑ ከሉዊስቪል ሙሐመድ አሊ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መብረር በጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መከስከሱ ተመላክቷል፡፡
የኬንታኪ ግዛት አስተዳዳሪ አንዲ በሺዬር÷ የጭነት አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የመፈንዳት አደጋ እንዳጋጠመው አስረድተዋል፡፡
በተከሰተው አደጋም እስካሁን የ7 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን ÷11 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል፡፡
የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁመው÷ የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
አደጋውን ተከትሎ የተፈጠረውን የእሳት አደጋ በፍጥነት መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የበረራ ቁጥሩ 2979 የሆነው የጭነት አውሮፕላን 38 ሺህ ጋሎን ነዳጅ ጭኖ ወደ ሆኖሉሉ ሊያቀና እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
