የሕንድ ትልቁ አየር መንገድ ኢንዲጎ ከፍተኛ ቀውስ ገጥሞታል፣ ከማክሰኞ ጀምሮ ከ300 በላይ በረራዎች ተሰርዘዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞችም በአገር አቀፍ ደረጃ በረራ እንዲስተጓጎልባቸዉ ሆኗል።ዴሊ፣ ሙምባይ፣ ሃይደራባድ እና ቤንጋሉሩ በህንድ ውስጥ ከፍተኛ የመንገደኞች መጨናነቅ በሚታይባቸዉ አየር ማረፊያዎች የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
አየር መንገዱ ለተፈጠረው መስተጓጎል ቴክኒካል ብልሽቶችን፣ የአየር ሁኔታን እና አዲስ የሰራተኞች ዝርዝር ህጎችን ተጠያቂ አድርጓል። አየር መንገዱ ከ60 በመቶ በላይ የሀገር ውስጥ ገበያ ድርሻ ያለዉ ሲሆን ዋና ዋና ሜትሮ ከተሞችን እና ትናንሽ ከተሞችን ያገናኛል።ኢንዲጎ ችግሩን ለማረጋጋት እስከ አርብ ድረስ ባለው መርሃ ግብሩ ላይ “ማስተካከያዎችን” አድርጓል።
እንደ ኢንዲያን ታይምስ ዘገባ ሐሙስ ጠዋት ብቻ በዴሊ 33 በረራዎች ኢንዲጎ መሰረዙን ያስታወቀ ሲሆን በቦምቤ ወይም ሙምባይ 85 እንዲሁም 73 በረራዎች በቤንጋሉሩ መሰረዙን ዘግቧል።
የሕንድ አቪዬሽን ተቆጣጣሪ የተቋረጠውን ችግር በማጣራት ላይ ሲሆን አየር መንገዱ የተቋረጠውን እና የመዘግየቱን ምክንያት ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል።ከኖቬምበር 1 ጀምሮ ኢንዲጎ የበረራ ሰአታትን የሚገድብ እና ተጨማሪ እረፍት በሚሰጠዉ በአዲሱ የበረራ ህግ መሰረት የአብራሪ እና የበረራ መስተንግዶ ሰራተኞች እጥረት አጋጥሞታል ሲሉ የህንድ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች አመላክተዋል።
