ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2021 ወደ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ህጻናት ክትባት ያልወሰዱ እና ጀምረው ያቋረጡባት ቢሆንም በ2024 ግን ወደ 768 ሺህ ዝቅ ማለቱን በጤና ሚኒስቴር የብሔራዊ የክትባት ፕግራም የዴስክ አማካሪ ወ/ሮ ጸጋነሽ ገድሉ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ይሄ ቁጥር ቀላል የማይባል በመሆኑ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በጤና ባለሙያዎች እና በአስከታቢዎች መካከል ያለው ተግባቦት በቂ አለመሆን፣ እናቶች ስለ ክትባቱ ጥቅም አስፈለጊውን ግንዛቤ አለማግኘታቸው፣ ክትባቱ ስላለው የጎንዮሽ ጉዳት እና በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አለማወቅ ህጻናቱ ክትባት ጀምረው የሚያቋርጡባቸው መንስኤዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ፍትሃዊ የክትባት ሽፋን አለመኖሩ፣ የሰላም እጦት እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ፈተናዎች እንደሆኑም ገልፀዋል።
ወላጆች ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናትን በተገቢው ወደ ጤና ተቋማት በመውሰድ እንዲያስከትቡም አሳስበዋል።
