በኢትዮጵያ ላይ ከሚፈጸሙ የሳበር ጥቃት ከሙከራዎች መካከል ከፍተኛውን መጠን የያዘው ‘ሰርጎ ገብ’ የተሰኘው የሳይበር ጥቃት መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አስታወቀ።
ይህ የሳይበር ጥቃት በድረ ገጽ፣ በቁልፍ መሠረተ-ልማቶች እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ዒላማ ያደረገ እንደነበር የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሳይበር መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መሐመድ ፈረጃ ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት 13ሺህ 443 ጥቃቶችና የጥቃት ሙከራዎች መመዝገባቸውንም ተናግረዋል።
አክለውም በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እና ቁልፍ መሠረተ-ልማቶቹን በሚያሥተዳድሩ ተቋማት ጥረት 97 ነጥብ 16 በመቶ ለሚሆኑት የጥቃት ሙከራዎች ምላሽ ተሰጥቷል ብለዋል።
አቶ መሐመድ፣ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎቹ ቢሳኩ እንደሀገር ይደርስ የነበረው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የሳይበር ጥቃቶቹን በመቆጣጠር፣ የጉዳት መጠንን በመቀነስ፣ ድጋሚ ለጥቃት እንዳይጋለጡ ደኅንነታቸውን የማጠናከር ሥራ ተከናውኗል ሲሉ ገልጸዋል።
በቁልፍ መሠረተ-ልማቶች ላይ የሚቃጡ ዓይነተ-ብዙ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን በማክሸፍ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው አክለው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ዲጂታላይዜሽን ምክንያት በብዛት የሳይበር ጥቃቶች ኢላማ እየሆነች መምጣቷን ቼክ ፖይንት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂስ በ2025 የአፍሪካ የሳይበር ደህንነት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል።
ሪፖርቱ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ያሉ ድርጅቶች በሳምንት በአማካይ ከ3 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች እንደሚገጥማቸው አስታውቋል።
ከሀገራት መካከል ናይጄሪያ በብዛት ጥቃት ያስተናገደች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በሳምንት ከ11,000 በላይ የሚሆኑ ጥቃቶች ዒላማ በመሆን በከፍተኛ ሁኔታ የሳይበር ጥቃት ኢላማ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን የደቡብ አፍሪካው አይ አፍሪካ መዘገቡ ይታወሳል።
