በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና የሎዛ ድርሳናት(2017 ዓ.ም) ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ጥር 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍ ኤጄንሲ(ወመዘክር) ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ አዳራሽበድምቀትተመረቁ።
የመጻሕፍቱ መቼት በኢትዮጵያ ሚሊኒዬም ዋዜማ ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ የሚዘልቅ ሲሆን በገጸ ባህሪያቱ ሙግት በፍቅር፣ በባህልን እና ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ ይፈላሰፋል። የስደት ገጠመኞችን ያስቃኛል። በቀልብ አንጠልጣይ ትረካ የገጸ ባህሪያቱን መጨረሻ ለማወቅ እንደሚያጓጉ በመፅሐፍቶቹ ላይ ዳሰሳ ያቀረቡ ባለሙያዎች ምልከታና ሀሳባቸውን አስፍረዋል። የሎዛ ዘፀአት መፅሐፍ የገፅ ብዛት 557 እና የሎዛ ድርሳናት በ517 ገፆች የተቀነበቡ ናቸዉ።
ጥር 9 ቀን 2018 ዓ.ም.ከሰዓት በኋላ በተከናወነው የመፅሐፍ ምረቃ ላይ የግዮን መጽሔት ኤዲተር ጋዜጠኛና ተርጓሚ ሄኖክ ገለታው የሎዛ ድርሳናት መፅሐፍ ዳሰሳና ምልከታዉን አቅርቧል። በተጨማሪ በጋዜጠኛና ደራሲ ታምሩ ከፈለኝ የመፅሐፍ ዳሰሳ የቀረበ ሲሆን ተጋባዥ እንግዶች ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ደራሲት የዝና ወርቁ እና ደራሲት እየሩሳሌም ነጋ እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች አስተያየታቸውን አቅርበዋል።
ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና የሎዛ ድርሳናት(2017 ዓ.ም.) መፅሐፍቶች ሲመረቁ ልዩ ተጋባዥ እንግዶች ዝግጅቱ ላይ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ሰዎች የጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ ቤተሰቦች አብሮ አደጎች አድናቂዎች ወዳጆች ጥሪ የተደረገላቸው ታዳሚያን ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ዋዜማ ላይ የተመሰረተ፣ ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ የሚዘልቅ የስደት ታሪክን፣ ፍቅርን፣ ባህልን እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ በእዉነተኛ ታሪክ የተመሰረተ ልብ አንጠልጣይ ልቦለድ መነጋገሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ፈር ቀዳጅ ድርሰቶችና በስደት ዓለም ዉስጥ ያለ ህይወት የተዘራባቸዉ እንደሆኑ ተብራርቷል።
ጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ በአጠቃላይ የአስገራሚ ታሪኮች ስብስብ የስደትን ህይወት የሚተርክ መጽሀፍ ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ብቅ ማለት የቻለ በስደት በህይወት በስራ ዓለም በርካታ መከራዎችንና ዉጣዉረዶችን ያለፈ ያልተዘመረለት ጋዜጠኛና ደራሲ ሲሆን የነጻው ፕሬስ ፍሬና ትሩፋትም ነዉ።
