በኢትዮጵያ ዱቄት እና የዱቄት ውጤቶች ማምረት ላይ የሚገኙ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን በበቂ ሁኔታ ወደ ገበያ ለማቅረብ የነዳጅ እጥረት ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው አስታውቀዋል ።
የዘርፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ዱቄት እና የዱቄት ውጤቶች አምራቾች ማኅበር ትላንት ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው 17ኛው መደበኛ ጠቅላይ ጉባኤው ላይ ነው ።
በጉባኤው ወቅታዊው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ምርቶችን ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ በወቅቱ ለማድረስ እንቅፋት እንደሆነ ተብራርቷል።
የነዳጅ እጥረቱ በኢንዱስትሪዎቹ የምርት ሂደትና በሥርጭት ሰንሰለቱ ላይ ጫና ማሳደሩን አንዳንድ የማኅበሩ አባላት አንስተዋል ።
በጉባኤው ንግግር ያደረጉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ተድላ ኃይለጊዮርጊስ ማኅበራቸው ከመንግስት ጋር በመሆን፣ የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን ጨምሮ በዘርፉ የታዩ ሌሎች ማነቆዎችን ለመፍታት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ዘርፉ በንጥረ ነገር የበለጸገ የስንዴ ዱቄት ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም የኢንዱስትሪውን ዕድገት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዱቄት እና የዱቄት ውጤቶች አምራቾች ማኅበር ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችን በማደራጀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ አጠቃላይ የሥራ ክንውን ሪፖርትና ነባራዊ ፖሊሲዎች ላይ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል።
ማኅበሩ በዱቄት ምርት ራስን ለመቻልና የሥነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በኢንዱስትሪዎቹ መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።
