የግብይት መጠኑ በአምስት ወራት ብቻ በእጥፍ እንደሚያድግ ይጠበቃል
በባንኮች መካከል የሚከናወነው የአንድ ቀን የገንዘብ ገበያ ግብይት በዚህ ሳምንት ባሳየው እጅግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ግብይቱ ከተጀመረበት ያለፈው አመት ወዲህ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ማስመዝገቡ ተገለጠ።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ባወጣው ሳምንታዊ ሪፖርት መሠረት፣ ካለፈው ሰኞ የካቲት 16 ጀምሮ ባሉት አምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ብቻ በባንኮች መካከል የ87.4 ቢሊዮን ብር በአንድ ቀን/overnight maturity ግብይት ተፈጽሟል።
ይህ አኃዝ በገበያው ታሪክ በአንድ ሳምንት ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛው የገንዘብ መጠን ሲሆን፣ በሳምንቱ ውስጥ በአጠቃላይ 125 በአንድ ቀን ተመልሶ የሚከፈል የገንዘብ ልውውጥ ስምምነቶች መከናወናቸውንም ሪፖርቱ ያመለክታል።
ይህም ቀደም ሲል በጥር ወር መጨረሻ ተመዝግቦ የነበረውን የ53 ቢሊዮን ብር ክብረ ወሰን በከፍተኛ ልዩነት የሰበረ ስኬት ሆኗል።
ይህ አስደናቂ ዕድገት ሊመዘገብ የቻለው በዘመናዊው የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ የባንኮች መተማመን በመጎልበቱና ተቋማቱ በገበያው ላይ ያላቸው ልምድ እየዳበረ በመምጣቱ እንደሆነ ተገልጿል።
በተለይም ቀደም ሲል የሰባት ቀን ግብይቶች ይይዙት የነበረው የበላይነት ተቀይሮ፣ ባንኮች ለዕለት ተዕለት የገንዘብ ፍላጎታቸው ማሟያ የሚጠቀሙበት የአንድ ቀን ግብይት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱ የገበያውን መነቃቃት ያሳያል ተብሏል።
ጥቅምት 2017 ዓ.ም የተጀመረው ይህ የባንኮች መካከል የገንዘብ ገበያ ባለፈው መስከረም 2018 ዓም አንድ ትሪሊየን ብር ያለፈ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ግብይት እጥፍ ማለትም ሁለት ትሪሊየን እንደሚያል ይጠበቃል፡፡
በዚህ ሳምንት የተደረገውን ግብይት ጨምሮ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የተከማቸ የግብይት መጠኑ 1.96 ትሪሊዮን ብር ላይ መድረሱ ነው የታወቀው፡፡
