ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የተገደሉባት ኢራን በቀጣይ ማንን በጠቅላይ መሪነት ትመርጣለች የሚለው ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው ለመገናኛ ብዙኃን ተናገሩ።
ትራምፕ ከዜና ምንጮቹ ሮይተርስ እና አክሲዮስ ጋር ባደረጓቸው የተለያዩ ቃለ መጠይቆች፤ ቀጣይ መሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቁት የአያቶላህ ኻሜኒ ልጅ ወደ ሥልጣኑ እንዲመጡ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ፤ ባለፈው ታህሳስ ላይ ወደ ቬንዙዌላ ገብተው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ከያዙ በኋላ እንዳደረጉት ሁሉ የኢራን ቀጣይ መሪ የመምረጥ ሂደት ላይ ራሳቸው መሳተፍ እንደሚፈልጉ መናገራቸውን የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ዘግቧል።
ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ደግሞ “ከኢራን ጋር ሆነን [ቀጣዩን መሪ] መምረጥ ይኖርብናል። ያንን ሰው መምረጥ ይኖርብናል” ብለዋል።
ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸውን ከተረጋገጠ በኋላ ቀጣዩ መሪ ማን ይሆናል የሚለው ሲያነጋግር ቆይቷል። የቀድሞው መሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ቀጣዩ መሪ እንደሚመረጥም ተነግሯል።
ሥልጣኑን እንደሚረከቡ ከሚጠበቁት መካከል ስማቸው ተደጋግሞ እየተነሱ ያሉት የቀድሞው አያቶላህ ልጅ ሞጅታብ ኻሜኒ ናቸው። ትራምፕ ከአክሲዮስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኻሜኒ ልጅ የጠቅላይ መሪነቱን ሥልጣን እንዲቆናጠጡ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
“ለእኔ የኻሜኒ ልጅ [ሥልጣኑን መረከቡ] ተቀባይነት የለውም። የምንፈልገው ለኢራን ስምምነት እና ሰላምን የሚያመጣ ሰው ነው” ብለዋል።
ትራምፕ፤ “ጊዜያቸውን እያባከኑ ነው። የኻሜኒ ልጅ ያንን ያህል [ፖለቲካዊ] ክብደት የለውም። በቬንዙዌላ ከዴልሲ [ሮድሪጌዝ] ጋር እንደነበረው ሁሉ ሹመቱ ውስጥ መሳተፍ አለብኝ” ሲሉም ተናግረዋል።
የአያቶላህ ኻሜኒን ፖሊሲዎችን የሚያስቀጥል አዲስ መሪ እንደማይፈልጉ ለአክሲዮስ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህ አይነት ሰው ወደ ሥልጣኑ የሚመጣ ከሆነ “በአምስት ዓመት ውስጥ” አሜሪካ ተመልሳ ወደ ጦርነት እንድትገባ እንደሚያስገድዳት ጠቅሰዋል።
ትራምፕ ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታም በተመሳሳይ “በየአምስት ዓመቱ ተመልሰን ይህንን [ጦርነት] ደጋግመን እንዳናደርግ፤ ኢራንን ወደፊት የሚመራውን ሰው በመምረጥ ሂደት ውስጥ መሳተፍ እንፈልጋለን። ለሕዝቡ እና ለአገሪቱ ታላቅ የሚሆን ሰው እንፈልጋለን” ብለዋል።
የቀድሞውን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒን ለመተካት ቀዳሚ ዕጩነት ሆነው የወጡት ልጃቸው ሞጅታብ፤ ቀጣይ መሪ የመሆን ዕድላቸው አነስተኛ ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል።
BBC
