ሪያድ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ — ሳዑዲ ዓረቢያ ለበርካታ አስርተ ዓመታት የቆየውንና የውጭ ዜጎች ንብረት እንዳይገዙ የሚከለክለውን ጥብቅ ሕግ በማሻሻል፣ ከዚህ ከ2026 የፈረንጆቹ ዓመት ጀምሮ አዲሱን የሪል እስቴት አዋጅ በተግባር ላይ ማዋሏን አስታውቃለች።
ይህ ታሪካዊ የተባለለት የኢኮኖሚ ለውጥ የሀገሪቱን የ2030 ራዕይ ለማሳካትና ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የታለመ ስትራቴጂ አካል መሆኑ ተገልጿል። የአዋጁ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡
- የግዢ ቀጠናዎች፦ የውጭ አገር ግለሰቦች እና ኩባንያዎች እንደ ሪያድ፣ ጅዳ እና ኒኦም ባሉ በመንግሥት በተለዩ የኢንቨስትመንት ቀጠናዎች ውስጥ ንብረት መግዛት ይችላሉ።
- ለመኖሪያ ቤት የተሰጠ ፈቃድ፦ በሳዑዲ ዓረቢያ በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ለግል መኖሪያ የሚሆን አንድ ቤት ከተፈቀዱ የኢንቨስትመንት ቀጠናዎች ውጭም ቢሆን መግዛት ተፈቅዶላቸዋል።
- የተከለከሉ ቦታዎች፦ መካ እና መዲና አሁንም ለውጭ ዜጎች ዝግ ሆነው የሚቀጥሉ ቢሆንም፣ ለሙስሊም የውጭ ዜጎች ግን ውስን የባለቤትነት መብቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
- ታክስና ክፍያ፦ የውጭ ዜጎች ንብረት ሲገዙ የ5 በመቶ የግብይት ክፍያና ተጨማሪ የዝውውር ታክስ የሚከፍሉ ሲሆን፣ አጠቃላይ ክፍያው እስከ 10 በመቶ ሊደርስ ይችላል።
- የነዋሪነት ፈቃድ (Premium Residency)፦ ቢያንስ 4 ሚሊዮን የሳዑዲ ሪያል የሚያወጣ ንብረት የገዙ የውጭ ዜጎች የፕሪሚየም ነዋሪነት ፈቃድ የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል።
ማንኛውም የቤትም ሆነ የመሬት ግዢ በሳዑዲ የሪል እስቴት ባለስልጣን ዲጂታል መድረክ በኩል መመዝገብ እንዳለበት በጥብቅ ታዟል። ይህ እርምጃ ሀገሪቱ በነዳጅ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስና ኢኮኖሚዋን ለማስፋፋት የምታደርገው ጥረት አካል መሆኑ ተመልክቷል።
