የቀድሞ ፕ/ት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የስንብት ቃል ለጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ!!
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
1. እንደ መንደርደሪያ
ግዮን መጽሔት :- የቀድሞ የሀገራችን ፕሬዚደንት የነበሩት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የፕሬዝደትነት ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አብዛኛው ጊዜያቸውን ‹‹በዕርቀ-ሰላም እና በአረንጓዴ ልማት›› ሥራ ዙሪያ ባዋሉበት ወቅት፤ ለተደጋጋሚ ጊዜያት ከክቡርነታቸው ጋር ለመገናኘትና ረዘም ያለ የቃለ-መጠይቅ ቆይታ ለማድረግ ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡
ከፕ/ት ግርማ ጋር ቆይታ ለማድረግ ምክንያት የሆነኝ ደግሞ ክቡርነታቸው ከርእሰ ብሔርነት ሥራቸው በኋላም የቀጠሉበት ‹የሰላም እና የአረንጓዴ ልማት› አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ እናም እርሳቸው በሰላም እና በአረንጓዴ ልማት ላይ እያከናወኑ ያሉትን ሥራዎቻቸውን በተመለከተ ለ94ኛ ዓመታቸው መታሰቢያ የሚሆን ፈረንጆቹ ‹‹Coffee Table Magazine›› በሚል የሚጠሩት ዓይነት ሥራቸውን የሚዘክር መጽሔት ለማዘጋጀት ኃላፊነት ወስጄ ስሠራ ነበር፡፡
ፕ/ት ግርማ ከርእሰ ብሔርነት ኃላፊነታቸው መጠናቀቅ በኋላም በተለይ በሰላም እና በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ ሰፊ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው አስቀጥለውት ነበር፡፡ እርሳቸው የደን/የአረንጓዴ ልማት ጉዳይ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ዋንኛ አጀንዳቸው ነበር፡፡ እንደውም ታሪክ እንደሚነግረን፤
መ/አ ግርማ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የፓርላማ አባል በነበሩበት ጊዜ በሀገሪቱ ‹‹የደን ሕግ›› እንዲወጣ ያደረጉ የአረንጓዴ ልማት ጠበቃ፤ የተፈጥሮ/የአካባቢ ጥበቃ ተቆራቋሪ ጀግና ነበሩ፡፡
ለክቡርነታቸው ከተፈጥሮ እኩል ለእርሳቸው የሰላም ጉዳይም ዋንኛና ተቀዳሚ አጀንዳቸው ነበር፡፡
ፕ/ት ግርማ፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ዕርቀ-ሰላም ይወርድ ዘንድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች፤ ከእነ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ቀዳሚ ሙፍቲ ኻጂ እንድሪስ፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ክ አባትና መሪ ከሆኑት ከብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ፣ ከወንጌላውያን አብያተ-ክርስቲያናት አባቶች፣ በኢትዮጵያና በወጪ አገራት ከሚኖሩ ኤርትራውያን ምሁራን፣ ከአገር ሽማግሌዎች፤ ከእናቶች፣ ከአባ ገዳዎች… ወዘተ. ጋር በመሆን በብዙ ለፍተዋል፤ ደክመዋል፡፡
ፕ/ት ግርማ ዕድለኛ ነበሩ፡፡ ፈጣሪ ዕድሜያቸውን አርዝሞላቸው በሕይወት እያሉ በብዙ የደከሙበት፤ የለፉበት የዕርቀ-ሰላም፣ የአረንጓዴ ልማት አጀንዳ ዕውን ሆኖ ለማየት በቁ፡፡ እናም በጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥረትና በጎ ፈቃድ የተነሳ ለሦስት ተከፍለው (የሀገር ቤቱ፣ ሕጋዊው እና ገለልተኛ) የነበሩትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ አባቶች ዕርቀ-ሰላም ለማየት ቻሉ፡፡
ክቡርነታቸው ለዕርቀ-ሰላሙ ስኬት በመኖሪያ ቤታቸውም ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት በላይ በስደት አሜሪካ አገር ለኖሩት ለፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ እና አብረዋቸው ከስደት ለተመለሱት ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት/አባቶች፤ ‹የእንኳን ደህና መጣችሁ!› አቀባባልና የምሳ ግብዣ አድርገውላቸው ነበር፡፡
በመቀጠልም፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ዕርቀ-ሰላም እንዲወርድ ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቶ በጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት፤ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ የዘለቀውን ቁርሾ በዕርቀ-ሰላም እንዲደመደም አደረጉ፡፡
በአዲስ አበባና በአስመራ ከተማ ጎዳናዎች በዘንባባ ዝንጣፊና በነጭ ርግብ ሲደምቁ፤ በኢትዮጵያውያንና በኤርትራውያን ወንድማማችና እኅትማማች ሕዝቦች የናፍቆትና የስስት እንባ የአስመራና አዲስ አበባ ጎዳናዎችን በደስታና በአንድነት ሲቃ ተውጠው ሲያነቡ – ይህን ብዙዎቻችንን ያስደሰተና ያስገረመ ታሪካዊ ትእይንት ክቡር ፕሬዚደንት በዓይናቸው ዐይተው፤ በጆሮአቸው ሰምተው በደስታ እንባቸውን አፍሰዋል፡፡
ፕ/ት ግርማ ይህን እርሳቸውና የሰላም አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸው ምኞት ተሳክቶ በማየታቸው በአካል እና በደብዳቤ ጭምር ለጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) የምስጋና የደስታ መግለጫ ቃል ልከው ነበር፡፡
2. የፕ/ት ግርማ የመጨረሻ ቃል ለጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ
ክቡርነታቸው ለዚህ ታላቅ ታሪካዊ ክስትት የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ በማሰብ ለክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የተላከውን ደብዳቤ የማርቀቅ ሥራ ኃላፊነቱን ለእኔ ነበር የሰጡኝ፡፡ ክቡርነታቸው በሰጡኝ ኃላፊነትና መመሪያ መሠረትም ለክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ የሚላከውን ደብዳቤ በጥንቃቄ አዘጋጅቼ ረቂቁን እርሳቸው እንዲያዩት በጸሐፊቸው በኩል ላኩላቸው፡፡
ክቡርነታቸው ደብዳቤው እንደደረሳቸው ስልክ ደወሉልኝና ነገ 4 ሰዓት ቢሮአቸው መምጣት እችል እንድሆን ጠየቁኝ፡፡ እኔም መምጣት እንደምችል ነግሬያቸው ተለያየን፡፡ ቀጠሮ ላይ ቀልድ የማያውቁት ፕ/ት ግርማ በነገታው 4 ሰዓት ቢሮአቸው ቀድመው ጠበቁኝ፡፡ የሰላምታ ልውውጥ ካደረግን በኋላ በቀጥታ ወደ ጉዳያቸው ገቡ፡፡
‹‹ደብዳቤውን አይቼዋለሁ በእውነቱ ግሩም ነው፡፡ የበዛ የቀይ ባሕር ናፍቆትና ስስት እንዳለብህ ግን አሳብቆብኻል›› አሉኝ በፈገግታ ታጅበው፡፡
ቀጠሉናም፤ ‹‹አየህ እኔ የኤርትራ ምድርን በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ምክንያት ለ20 ዓመት ቆይቼያለሁ፤ እናም ሕዝቡንም አገሩንም በሚገባ አውቀዋለሁኝ፡፡ ሊበጠስ የማይችል የጋራ ታሪክና ሥልጣኔ ያለን፤ በባሕል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ገመድ የተሳሰርን፣ በደምና በአጥንት የተዛመድን ወንድማማችና እኅትማማች ሕዝቦች ነን፡፡››
ፕሬዚደንቱ በረጅም ከተነፈሱ በኋላ በሐሳባቸው ወደ ኤርትራ ምድር/ወደ ቀይባሕር፣ ምፅዋ፣ አሰብ፣ ወደ ውቢቷ አስመራ የተሻገሩ በሚመስል የትዝታና የናፍቆት ዕይታ ዓይናቸውን ቡዝዝ አድርገው በሐሳብ ጭልጥ አሉ… ከጥቂት አፍታ በኋላም ንግግራቸውን ገታ አድርገው የግል ካዝናቸውን ከፈቱና አንድ ታሪካዊ ሰነድ አውጥተው ፊቴ ላይ ዘረጉት፡፡
ሰነዱ፤ የኤርትራ አንድነት ኃይሎች የጻፉት አንድ ምስጢራዊ ደብዳቤ፣ በወቅቱ የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት የንጉሠ ነገሥቱ አገናኝ መኮንን የጄ/ል ነጋ ኃይለሥላሴ ማስታወሻ/ Memoire፣ በተባባሩት መንግሥታት ውሳኔ መሠረት በኤርትራ የተካሄደውን ‹የሪፈረንደም ምርጫ› የሚያሳዩ የተለያዩ ፎቶግራፎችና ሌሎች ሰነዶች የተካተቱበት ነው፡፡
እነዚህን በጥንቃቄ የተያዙ ታሪካዊ ሰነዶች ክቡር ፕ/ት ግርማ እንዳየው ወደ ፊቴ ገፋ አደረጉልኝ… ክቡርነታቸውን አመስግኜ እንደ ታሪክ ተማሪ ሰነዶቹን በጥንቃቄ ማየት ጀመርኩ፡፡ በተለይም ኤርትራን ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል የደከሙ የአንድነት ኃይሎች ምስጢራዊ ደብዳቤ ላይ ዓይኖቼ ተተክለው ቀሩ፡፡
ጀግናው አሉላ አባ ነጋ፣ ባሻ አውአሎም፣ ሮም ድረስ ተሻግረው ከፋሽስት ጋር ተፋልመው ለኢትዮጵያ ነጻነት፣ አንድነትና ክብር ያላቸውን ቀናኢነት በተግባር የገለጸው ጀግናው ዘርዓይ ደረስ፣ በፋሽስት መንግሥት ከአውሮፕላን ላይ ተጥሎ እንዲሞት የተፈረደበት የጥቁር አንበሳ አመራር የነበረው ኤርትራዊው ኮ/ል በላይ ኃይለአብ… ታሪክ ስማቸውን በወር-ቀለሙ የከተበላቸው የነጻነት፣ የአንድነት ምልክቶች!!
3. የታሪካዊ ሰነዶቹ ዕጣ ፈንታ፤
በርግጥ ታሪካዊ ሰነዶቹ ታሪካዊና አገራዊ ፋይዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ወደፊት ትውልድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስለሆነው ነገር ለማወቅ፣ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ለሚፈልጉ የሚጠቅሙ ሰነዶች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የኤርትራ የአንድነት ኃይሎች ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል ያደረጉትን ጥረት የሚጠቁሙት እነዚህ ሰነዶች ለወደፊቱ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል እንዲሁም በአፍሪካ ቀጣና አገራት መካከል ለሚታሰበው በፌዴሬሽን አሊያም በኮን-ፌዴሬሽን አንድ የመሆን ሐሳብ የታሪክ ማስረጃ ናቸው፡፡
እነዚህን ታሪካዊ ሰነዶች በወቅቱ ፕ/ት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ – ለታሪክ ጥናትና ምርምር ይጠቅምሃል በማለት በአደራ አስረክበውኝ ነበር፡፡ እናም እነዚህ በእጅ የሚገኙ ሰነዶች ካላቸው አገራዊ ፋይዳ አንጻር ለታሪክ ጥናትና ምርምር ይውሉ ዘንድ በማሰብ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ለማስረከብ በዝግጅት ላይ እገኛለሁ፡፡ ለታሪካዊ ሰነዶቹ ርክክብም አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
የኮሚቴው አባላትም፤ የፕ/ት ግርማ ቤተሰቦችና ወዳጆች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የሰላም አምባሳደሮች፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች፣ የሕግ ምሁራን፣ የዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን፣ ትምህርታቸውን በአስመራ ዩኒቨርሲቲ የተከታሉ ኢትዮጵያውያን ማኅበር ተወካይ… ይገኙበታል፡፡
ኮሚቴው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፣ ከየኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም እና ከኢትዮጵያ ቤተ-መጻሕፍት እና ቤተ-መዛግብት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተከታታይ ስብሰባዎችን በማድረግ በርክክቡ ሂደት ላይ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡
በተጨማሪም ከእነዚህ ታሪካዊ ሰነዶች ርክክብ ጎን ለጎንም የቀድሞው የአገራችን ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ሰላም፤ ለአረንጓዴ ልማትና እንዲሁም ለአገርና ለወገን የዋሉትን በርካታ ታሪክ የማይዘነጋውን ትልቅ ውለታዎቻቸውን በሚመጥን መልኩ ትውልድ እንዲያስታውሳቸው የሚያደርግ አንድ ትልቅ መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ለማድረግ በዝግጅት ሂደት ላይ ነን፡፡
4. የቀድሞ ፕ/ት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የስንብት ቃል ለጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ!!
‹‹No War no Peace!›› በሚባል ሁኔታ ውስጥ ድንበራቸውን ዘግተው ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ – በጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ አማካኝነት በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ዕርቀ-ሰላም በወቅቱ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ ታላቅ የምስራች ነበር፡፡ ለዓመታት የተለያዩ ቤተሰቦች፣ የልብ ወዳጆች፣ ዘመዳሞች… በደስታ ሲቃ ታጅበው የተገናኙበት ትልቅ ታሪካዊ ትዕይንት ነበር ያ የሰላም ስምምነት፡፡
የአዲስ አበባ እና የአስመራ ጎዳናዎች በደስታ ሲቃ፣ በናፍቆት እንባ የደመቁበት!!
ይህንን ታሪካዊ ክስትት በዓይናቸው ለማየት የበቁት ፕ/ት ግርማ ለጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ በላኩት የደስታ መግለጫ ደብዳቤያቸው፤ ‹‹… በታሪክና በባሕል፣ በሃይማኖትና በቋንቋ ለተጋመዱት፣ በደምና በአጥንት ለተሳሰሩት ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ሕዝብ ይህ ታላቅ የምስራች ነው፡፡ የተበሰረው የዕርቀ-ሰላም መንገድ እስከ መጨረሻው የሰመረና የተዋበ ይሆን ዘንድ…›› ለጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ ልባዊ ምኞታቸውን ገልጸውላቸው ነበር፡፡
ፕ/ት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ይህን የዓመታት ድካማቸው የተቋጨበትን በኢትዮጵያ እና በኤርትራን የሰላም ስምምነት የተሰማቸውን ደስታቸውን ለማጣጣም – ለ20 ዓመታት በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት በቆዩባት ውቧ አስመራ የ95ኛ ዓመት ልደታቸውን ለማክበር በዝግጅት ላይ እያሉ ነበር ሞት የቀደማቸው፡፡
የአረንጓዴ ልማት ጀግና፣ የተፈጥሮና የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ፣ የሰላም እንደራሴ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይልና መከላከያ ባለውለታ፣ የፓርላማ አባል (ኢትዮጵያን የዓለም ፓርላማ አባል ያደረጉ)፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን መስሪያ ቤት ቀደምት ፋና ወጊ… የኢትዮጵያ ርእሰ-ብሔር የነበሩት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ- ለአገርዎና ለወገንዎ የዋሉትን ውለታ ትውልድ ሁሌም በክብር ያስታውሰዋል፤ እርስዎንም ይዘክርዎታል፡፡
ሰላም!!
