ገብሩ አስራት
ግዮን መጽሔት :-የመጽሐፉ ርዕስ፡- ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች
ደራሲ፡- ፍሬሕይወት ሳሙኤል የገጽ ብዛት፡- 282
የሕትመት ዘመን፡- 2018 ዓ.ም
አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል በፃፉት በዚህ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› መጽሐፍ በርካታ አስተያየቶች መስጠት ይቻላል፡፡ የመፅሓፉን ያኽል አዎንታዊ አስተያየቶችንና የተወሰኑ ጠንካራ ትችቶችን ማቅረብም ይቻላል፡፡ ሆኖም እኔ አስተያየት ለመስጠት የመረጥኩት በመፅሐፉ ክፍል ሦስት፣ ምዕራፍ አስራ ስድስት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብጥር በሂደት የአናሳ ብሔረሰቦችን ሚና የሚያሳንስ መሆኑ በሚለውና ተያያዥ ጉዳዮችን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ለመስጠት የፈለጉት የጉዳዩ ወቅታዊነትና አንገብጋቢነት ተገንዝቤ፣ ሰፊ ውይይት ሊደረግበት ይችላል ከሚል በመነሳት ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ይደረጋል እየተባለ ስለሆነም በዚህ ጉዳይ አስቀድሞ መወያየቱ ይበልጥ ጠቃሚነት ይኖረዋል የሚል እምነትም ስላለኝ ነው፡፡
መነሻዬ ደራሲው የሰነዘሩት አሁን ባለው ሕገ መንግሥት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብጥር አናሳ /minority/ ወይም አነስተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ብሔረሰቦች በሂደት በአገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው የመወሰን ሥልጣን ዝቅተኛና እዚህ ግባ የማይባል ይሆናል፤ የሚለው ሐሳብ ነው፡፡ ይህ የሆነውም ሕገ መንግሥቱ ሲጠነሰስና ሲፀድቅ አንስተኛ የሕዝብ ብዛት ላላቸው ብሔረሰቦችና ክልሎች ትኩረት ባለመስጠቱ ነው የሚለውን የደራሲው ምልከታ እጋራለሁ፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 61፡ ንኡስ አንቀፅ 2፡ እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም የብሔር ወይም ብሔረሰቡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ተወካይ ይኖረዋል፡፡ ይላል፡፡
ደራሲው በመፅሐፋቸው እንዳመለከቱት ከ19 ዓመት በፊት ወይም በ1999 ዓ.ም በተደረገው የመጨረሻው ሕዝብ ቆጠራ መሰረት ትላልቅ ከሚባሉት ብሔሮችና ክልሎች መኻል ኦሮሚያ 25,363,756 አማራ 19,878,199 ሕዝብ ነበራቸው፡፡ በአንፃሩ 64 ብሔረሰቦች እያንንዳችው ከአንድ ሚልዮን በታች፣ አምሳ ብሔረሰቦች እያንዳንዳቸው ከ100,000 በታች፣ ሰላሳ ያህሉ ብሔረሰቦች እያንዳንዳቸው ከ20,000 በታች፣ ሃያ የሚያህሉት ደግሞ ከ10,000 በታች የሕዝብ ብዛት ነበራቸው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የውክልና ስሌት መሰረት በወቅቱ ከነበረው አጠቃላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 153 መቀመጫዎች ኦሮሚያ ሃያ ስድስቱን አማራ ደግሞ ሃያውን ተቆጣጥረው ነበር፡፡ ሁለቱ ክልሎች ብቻ 46 መቀመጫዎች ነበ ቸው፡፡ በወቅቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከነበሩት 69 ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ 64ቱ እያንዳንዳቸው ከአንድ ሚለዮን ሕዝብ በታች ስለነበራችው የተወካዮቻቸው ብዛት 64 ነበር፡፡
ደራሲው በትክክል እንዳስቀመጡት ከሆነ አሁን 50,000 ሕዝብ ያላቸው ብሔረሰቦች አንድ ተጨማሪ ተወካይ ለማግኘት 800 ዓመታት መጠበቅ ሲኖርባቸው አሁን 25,000 ሕዝብ ያላቸው ደግሞ 1000 ዓመታት መጠበቅ ይኖረባቸዋል፡፡ በአንፃሩ ከፍተኛ ሕዝብ ብዛት ያሉዋቸው ኦሮሚያና አማራ አንድ ሚልዮን ሕዝብ ለመጨመር የሚስፈልጋቸው ጊዜ አጭር ይሆንና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚኖራቸው ውክልናና ተፅአኖ ይበልጥ ይጨምራል፡፡
በቅርቡ በወርልድ ሜትር በወጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ግምት እንደተመለከተኩት ጠቅላላ ቁጥራችን ከ137.5 እስከ 138.9 ደርስዋል፡፡ ይህም በ1999 ዓ.ም ከነበረው 73,750,932 ጋር ሲነፃፀር ወደ እጥፍ የተጠጋ ሆኗል፡፡ በዚህ አዲሱ ግምት የኦሮሚያ ሕዝብ ብዛት 40,884,000 የደረሰ ሲሆን የአማራ ደግሞ 30,216,000 ደርስዋል፡፡ እንግዲህ ባለፉት 19 ዓመታት ውስጥ ኦሮሚያ 15 ሚልዮን ሲጨምር አማራ ደግሞ 11 ሚልዮን ጨም ል፡፡ ከነዚህ ቀጥለው ብዙ ሕዝብ ኣላቸው የሚባሉት ትግራይ 2 ሚልዮን፣ ሶማሊያም እንዲሁ 2 ሚልዮን ሲጨምሩ ሲዳማ ደግሞ 3 ሚልዮን ጨም ል፡፡ በመሆኑም ሁለቱ ትላልቅ ክልሎች በፌዴረሽን ምክር ቤት የሚኖራቸው ውክልና በ26 ሲያድግ ሦስቱ መለስተኛ ክልሎች ደግሞ 7 ተወካዮችን ጨምረዋል፡፡ ካለው ለውጥ በመነሣት ደራሲው ከገመቱት ሁለት ትውልድ ቀድሞ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለት ወይ በሶሰት ክልሎች አብላጫ ድምፅና ቁጥጥር ስር ይሆናል ማለት ነው፡፡
ይህን ጉዳይ እያነሳሁ ያለሁት ብዙ ሕዝብ ያላቸውን ብሔሮች ወይም ክልሎች ለኢትዮጵያ ትልቅ ፀጋ መሆናቸውን ዘንግቼ አይደለም፡፡ ጉዳዩን እያነሳሁ ያለሁት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ምክር ቤት ነው ከተባለ የሚኖራቸው ውክልናም ፍትሓዊ መሆን ይኖረበታል ከሚል ነው፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ብሔር ብሔረሰቦችን እንዲሁም ክልሎችን አንዱ ከሌላው አብልጦ ውክልና የሰጠ በመሆኑ ከፍትሕ አንፃር ተቃርኖ ያለው ነው፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ብዙ ሕዝብ ያለው የገዘፈ ውክልና ጥቂት ሕዝብ ያለው ደግሞ ያነሰ ውክልና ካለው ከጅምሩ ኢፍትሐዊነትን ያነገሠ ሆኗል፡፡ የውክልና መርሑ እያንዳንዱን ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይ ክልል የራስ ማንነት /identity/ ያለው አሐድ አንጂ በቁጥር ወይም በአሃዝ የሚመዘን መሆን የለበትም፡፡ አንድ ሰው ቢረዝምም ቢያጥርም፣ ቢከሳም ቢወፍርም፣ ቢደኸይም ቢበለፅግም በመብቶቹ ጉዳይ ልዩነት አይፈጠርም፡፡
ይህ መርሕ ሕጋዊ ዕውቅና ላላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ክልሎችም የሚሠራ መሆን ይኖርበታል፡፡ አልፎ አልፎ ከሊሂቃን የምሰማቸው ብሔሮች ወይም ክልሎች በወርዳቸውና በቁመታቸው ሊወከሉ ይገባል የሚለው አሰተሳሰብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተግባራዊ ከተደረገ በቋሚነት ያልተመጣጠነ የስልጣን ሚዛን /asymmetric power/ ስለሚፈጥር ኢዴሞክራሲያዊና ኢፍትሐዊ ሆኖ በፌዴሬሽኑ አንድነት ላይ አደጋን የሚደቅን ይሆናል፡፡ በእርግጥ የፓርቲዎች ውክልና መሠረቱ በሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዜጎች ወይም በሕዝብ ብዛት መወከሉ አግባብነት ያለው ነው፡፡ ይህን ስልም የብዝኃ ፓርቲ ውድድርና ውክልናን ታሳቢ በማድረግ እንጂ አሁን ባለው ከሞላ ጎደል የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ታሳቢ በማድረግ አይደለም፡፡
ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና ሳልወጣ ደራሲው አዲስ አበባንና ድሬዳዋን በተመለከተ ያነሡት ጉዳይ አለ፡፡ በአሁኑ ሕገ መንግሥታዊ ከክልል አወቃቀር ውጭ ሆኖው የተደራጁት እነዚህ ሁለት ከተሞች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክለና የላቸውም፡፡ በማንኛውም ክልል መስተዳደር ሥርም አይደሉም፡፡ ተጠሪነታቸው ለፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ ፀሐፊው እንዳሉት እነዚህ ከተሞች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከአገሪቱ አጠቃላይ ገቢ ከ50% በላይ የሚያመነጩትና ከፍተኛ ምሁራዊ ዓቅም ያላቸው እነዚህ ከተሞች የአገሪቱን የበጀት ድልድል በሚያፀድቀው ምክር ቤት አለመወከል ፍትሐዊም ተገቢም አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በክልሎች መኻል የሚነሱ ክርክሮችን የመወሰን፣ የመገንጠል ጥያቄዎች ሲነሱ የማስተናገድና ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ካለው ተቋም መገለላቸው የነዋሪዎቻቸውን ጥቅም የሚጎዳ ይሆናል፡፡ ስለሆነም በተለይ አዲስ አበባ የክልል ያህል ስልጣን ተሰጥቶት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይካተት የሚለው ሓሳብ ተገቢ ሆኖ የድሬዳዋ ጉዳይም በአንዱ ወይም በሌላዊ መልኩ መፍትሔ አግኝቶ ውክልናው መከበር ይኖርበታል፡፡
የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አወካከል በተመለከተ ከቀረበው አስተያየት በተጨማሪ መነሳት ያለበት አንር ጉዳይ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥልጣን ወሰን የሚመለከት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴረሽን ምክር ቤት ከሌሎች ተመሳሳይ የአስተዳደር ዘይቤ ከሚከተሉ አገሮች በተለየ ሁኔታ ስልጣኑ ተገድቦ ይገኛል፡፡ የስልጣን ወሰኑ በጣም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ መገደቡ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 60 ቁጥር 1 ላይ የሰፈረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉአላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው የሚለውን ድንጋጌ የሚቃረን ሆኖ ይታየኛል፡፡ በመሆኑም የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ውክልና ያለውን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ያለ ምንም ገደብ ሕግ የማውጣትና የማፅደቅ ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል፡፡ ደራሲው በዚህ ጉዳይ ላይም ተመሳሳይ አቋም ማንፀባረቃቸውን የምቀበለው ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕግ የማውጣት ሥልጣን መጎናፀፉ በተወካዮች ምክር ቤት የሚወጡትን ሕጎችና ውሳኔዎች ከክልሎች ወይም ከብሔር ብሔረሰቦች ጥቅም ጋር ያለመጣረሳቸው ለመቆጣጠር የሚረዳ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወከሉትን አካላት ጥቅም የሚያንፀባርቁ ሕጎችን ለማመንጨት ያስችለዋል፡፡ ከዚሀ በተጨማሪ አሸናፊው ፓርቲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፈለገውን ሕግ አያወጣ እንዳይፎልል የመቆጣጠሪያ ልጓም ሊሆን ይችላል፡፡
ከዚህ ምዕራፍ እይታ ውጭ የሆነው ሌላው ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም ባለቤት እንዲሆን የተሰጠውን ስልጣን የተመለከተ ነው፡፡ በአሁኑ ሕገ መንግሥት መሰረት ይህ ስልጣን ለፌዴረሽን ምክር ቤት መሰጠቱ ምክር ቤቱ የሕግ አውጭነት ተግባሩን በሚገባ እንዳይሳካ በማድረግ ወደ ፍርድ ቤት የሚቀይረው ሆኗል፡፡ ሲጀመር የፖለቲካ ውክልና እንጂ የሕግ እውቀትና ችሎታ የሌላቸው ተወካዮች ዋናው ሥራቸውን ትተው በማያውቁትና ሙያቸው ባልሆነ ጉዳይ በመሰማራት ከሁለቱም ሳይሆኑ ያስቀራቸዋል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ስልጣን በሙያው ለተካኑና የፖለቲካ ውግንና ለሌላቸው በፍትሐዊነት ለሚወከሉ ዳኞች ተሰጥቶ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ሕግ ወደ ማውጣትና ማፅደቅ ተግባር ቢሸጋገሩ ይሻላል እላለሁ፡፡
ፀሓፊው ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ተግባር ለልዩ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ወይም ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች ቢሰጥ ሲሉ ያቀረቡት ሓሳብ በከፊል የምጋራው ነው፡፡ ለልዩ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ቢሰጥ የሚደገፍ ሲሆን በመደበኛ ፍርድ ቤቶች መታየቱን ግን አልደግፈውም፡፡ ምክንያቱም በሕገ መንግሥት ዙሪያ የሚነሱ ክርክሮችና ውሳኔዎች ከግለሰብ በላይ የሚሄድ ውጤት ስለሚኖራቸው በሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ በቂ እውቀትና ችሎታ ባላቸው የሕግ ባለሙያዎች መዳኘቱ ይበልጥ ውጤታማ ሊያደርገው ይችላል ባይ ነኝ፡፡
ፀሐፊው በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውክልናና ሥልጣን ዙሪያ በቂና አሳማኝ መከራከሪያዎችን በማቅረብ የሕገ መንግሥት ለውጦች እንዲደረጉ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ሆኖም በኔ እይታ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወይም የክልሎች ውክልናና ሥልጣን ጉዳይ ከሕግ አውጭው ባሻገር ባሉት የፌዴራል ተቋማትም ጭምር ቢዳስሱ ይጠቅማል ባይ ነኝ፡፡ ከነዚህ መኻል እጅግ ወሳኝ በሚባሉት በሥራ አስፈፃሚው፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ በመከላከያና ደህንነት፣ በፍትሕ አካላት፣ እንዲሁም በተለያዩ ወሳኝ ኮሚሽኖች የሚኖራቸው ተሳትፎ በሚገባ ሊጤን ይገባል ባይ ነኝ፡፡ እነዚሀ ተቋማት በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ስለሚያሳድሩ ፍትሐዊ ተሳትፎ ከሌለ በአንድ ፓርቲ ወይም በአንድ ክልል ቁጥጥርና ተጽዕኖ ስር ውለው ሌላውን ባይተዋርና የበይ ተመልካች ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ይህን ስል ግን ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ አንደኛ እነዚህ ተቋማት ለተሳተፎ ሲባል ዕውቀትና ችሎታ በሌላቸው ሰዎች የሚሞሉ ሳይሆን ለስራው ተገቢ መስፈርት ማሟላታቸው ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ሁለተኛው ፍትሐዊ የማመጣጠንና የማሳተፍ ተግባር እንዲሁ በዘፈቀደ የሚኪያሄድ ሳይሆን ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንደሆነም ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
ለማጠቃለል በእኔ እይታ አሁን በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የግለሰብ እና የቡድን መብቶች መሳ ለመሳ የሚሄዱ እንጂ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ መሄድ አይቻልም፡፡ ዋናው ችግር እነዚህን በአንድ በኩል አብረው የሚሄዱ በሌላ በኩል ደግሞ ሊጣረሱ የሚችሉ መብቶች እንዴት አስታርቆ መሄድ እንደሚቻል ማስላትና ማገናዘብ አለመቻል ነው፡፡ እሰከ አሁን ድረስ ይህን ሚዛን ማስጠበቅ ባለመቻላችን በብዙ ጉዳዮች ላይ ሳንስማማ እየተጓዝን እንገኛለን፡፡ እንደያውም የሁለቱ ፅንፎች ሽኩቻ አይሎ ማስታረቁ አቅቶናል፡፡ ሁለቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች አሁንም መፍትሄ አላገኙም ባይ ነኝ፡፡
አንዳንድ ብሔር ብሔረሰቦችና ክልሎች በፌደራል መንግሥቱ በሚገባ አልተወከልንም በአካባቢያችንም በቂ የመወሰን ስልጣን አላገኘንም የሚሉ ጥያቄዎች እያነሱ ሲሆን የግለሰብ መብት አራማጆች ደግሞ ሕገ መንግሥቱ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እንጂ የግለሰብን መብት መሰረት ተደርጎ አልተቀረፀም የሚል ቅሬታ አላቸው፡፡ ሁለቱም መፈተሸ ያለባቸው ተገቢ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ አቶ ፍሬሕይወት በመጽሐፉቸው ለመመለስ የሞከሩትም ይህን ሚዛን አስጠብቆ የመሄድ ጥያቄን ነው፡፡ አቶ ፍሬ ሕይወት ሕገ መንግሥቱን መርምረውና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አገናዝበው ያቀረቧቸው ምክረ ሓሳቦች እጅግ ጠቃሚ ስለሆኑ ከእንግዲህ ባለቤቶቹ ሁላችንም ነን፡፡ ይህን ስል ግን ያገሪቱ ሊሂቃንና ሕዝቡ በሚገባ ተወያይቶባቸው በድርድር ካልተቋጩ ተግባራዊነታቸው ጊዜ እንደሚወስድ እገምታለሁ፡፡
—
ማስታወሻ፡-አቶ ገብሩ አስራት የህወሓት መሥራችና ነባር ታጋይ፣ ድርጅቱ በመርኅ ደረጃ መስማማት ተስኖት ለሁለት እስኪሰነጠቅ ድረስም የትግራይ ክልል የመጀመሪያው ርዕሰ መስተዳድር በመኾን ሰርተዋል፡፡ ከፓርቲው ተገፍተው ከወጡ በኋላም፣ ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር ‹‹አረና ትግራይ›› የተባለ ፓርቲን መሥርተው በሠላማዊ መንገድ ለዓመታት ትግሉን ቀጥለዋል፡፡ አቶ ገብሩ ‹‹ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ለታሪክና ለአካዳሚያው ዓለም ጠቃሚ የኾነ መጽሐፍ ጽፈው ያስነበቡም ሲኾን፣ አሁን ላይ በትግራይ ክልልና በአጠቃላይ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ አካሔዶችና እንቅስቃሴዎች ዙርያ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን በመቅረብ አስተያየቶቻቸውን ያቀርባሉ፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 230 መጋቢት 2018 ዓ.ም
