ሩሲያ በምትቆጣጠረው የዩክሬን ግዛት አውቶብስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን እና አስራ አንድ መቁሰላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ክሬምሊን በዩክሬን ምሥራቃዊ ዶኔትስክ ክልል የሾመቻቸው ዴኒስ ፑሺሊን ጥቃቱ ከሞስኮ ወደ ክሬሚያ ሲምፎሮፖል ይጓዝ በነበረ አውቶቡስ ላይ ረቡዕ ማለዳ መድረሱን ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና ረቡዕ ማለዳ በሴይንት ፒተርስበርግ ጭስ የታየ ሲሆን፣ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የከተማዋ የነዳጅ ማከማቻ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ሩሲያ ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚክ ፎረም በምታዘጋጅት ወቅት ነው።
ሩሲያ ትናንት ማክሰኞ በዩክሬን ከተሞች ላይ በርካታ የድሮን ጥቃቶች ፈጽማ ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 22 ሰዎች ተገድለዋል።
ፑሽሊን በድሮን ጥቃት በደረሰበት አውቶብስ ሰባት ሰዎች መግደላቸውን ገልጸው ጉዳት የደረሰባቸው 11 ሰዎች የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።
ዩክሬን በአውቶቡስ ላይ ስለተፈጸመው የድሮን ጥቃት እስካሁን ያለችው ነገር የለም።
ሩሲያ ሌሊቱን ከዩክሬን የተነሱ 350 ድሮኖችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።
