በዛሬው ዕለት መግለጫ የሰጠጡት የሰላም ሚኒስተር የአርሲውን ጥቃት ሃይማኖታዊ አይደለም ያለ ሲሆን በጉዳዩ ላይም ከሀይማኖት አባቶች ግራ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል። በተመሳሳይ ከሁለት ቀናት በፊት የኦሮሚያ ክልል፣ በትናንትናው ዕለት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ዛሬ ደግሞ የሰላም ሚኒስቴሩ“የአርሲው ጥቃት ሃይማኖት ተኮር አለመሆኑን” ገለፀዋል።
በአርሲ እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በንጹኃን ዜጎች፣ በፀጥታ አካላትና በእምነት ተቋማት ላይ የተፈጸሙትን አሳዛኝ የሽብር ጥቃቶችን መንግስት በጽኑ እንደሚያወግዝ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀዋል።
የሰላም ሚኒስተር ሙሀመድ እዲሪስ ሰሞኑን ከኦርቶዶክስ ሀይማኖት አባቶች ጋር ከተወያዩ በኃላ በዛሬ ዕለት በሰጡት መግለጫዎች በአርሲ የተፈፀመው ግድያ እና መፈናቀል ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው ሳይሆን ምርጫውን ለማደናቀፍ የተደረገ የሽብርተኞች ጥቃት ነው ብለውታል።
ሚነስተሩ አክለውም እርሳቸው በተወዳደሩበት ጎንደር ከተማ በጎንደር ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች ላይ የተፈፀመውን የቦንብ ጥቃት በማውገዝ የ አንድ ተማሪ ህይወት እንድያልፍ ምክንያት ሁኗል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በሰራችው ዘገባ ሁለት ተማሪዎች ህይወታቸው ማለፋን ከቦታው ባገኘችው መረጃ መሰረት መዘገቧ ይታወሳል። በሁለቱም ቦታዎች ለተፈፀሙት ጥቃትም “ የሸኔ” እና “ፅንፈኞች ” የፈፀሙት መሆኑን ተገልጿል።
የሰላም ሚኒስተር ከተቋቋመባቸው አላማዎች ውስጥ ለአካባቢያዊ ግጭቶች መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን በጥናት ይለያል፤ ኅብረተሰቡ ወደ ግጭትና አለመረጋጋት እንዳያመራ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያመለክት ጥናት የሚያቀርብ ሲሆን ግጭቶች ሲከሰቱ በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ ማስተባበርና መምራት የሚለው አንዱ አቋሙ ነው።
ከሀይማኖት ጋር በተያያዘም በሃይማኖት፣ በብሔርና ሌሎች ምክንያቶች ሽፋን የሚደረግ የአክራሪነትና የጽንፈኛነትን አስተሳሰብ ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን ለመቀየስ እና ለማስፈፀም የቋቋመ ተቋም ነው።
ሚኒስተሩ አክለውም ሀገራዊ ለውጡንና የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ ተስፋ የቆረጡ ጽንፈኛ ኃይሎችና የውጭ ጠላቶች የኢትዮጵያን ሰላምና የሕዝብ አብሮነት ለማፍረስ “አደገኛ የትንኮሳ ካርዶችን እየመዘዙ ” መሆኑን ሲሉ አንስተዋል።
የፀጥታ አካላት የምርጫውን ሂደት በመጠበቅ ላይ ባሉበት ወቅት፣ የሽብርተኛው የሸኔ ቡድን በአርሲ ዞን አስኮ ወረዳ ደለታ ጨፋ ቀበሌ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ያብራሩት ሚኒስትሩ፥ በጥቃቱ ወቅት በአካባቢው ሕዝብ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በጀግንነት የተዋጉ አምስት የሚሊሻ እና ሦስት የፖሊስ አባላት መስዋዕት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስተሩ ቀጥለውም ይህ እኩይ ተግባር በወረዳው አራት ሲቪል ዜጎች የተገደሉ ሲሆን አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ተቃጥሏል ብለዋል። በተጨማሪም አንድ የጤና ተቋምና የቀበሌ ጽሕፈት ቤት በታጣቂዎቹ ሲዘረፉ፣ 65 የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች በመቃጠላቸው ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል ብለዋል።
ከዚህ መደበኛ ጥቃት ውጭም በሽርካ ወረዳ ታግተው የነበሩ ሁለት ነዋሪዎች እንዲሁም በህንቆሌ ዋቤ ወረዳ ገንዘብ አምጡ ተብለው የታገቱ ሁለት ንጹሃን ዜጎች በታጣቂዎቹ ተገድለዋል።
ሰዎች ተበድለውና አጥፍተው እንኳን ቤተክርስቲያን እና የሃይማኖት ተቋማት ይጠለላሉ እንጂ እነዚህ ስፍራዎች የጥቃት ማዕከል መሆን ታሪካችንንም ሆነ እሴታችንን አይገልጽም ያሉት መሐመድ መንግሥት ይህን አሳዛኝ ድርጊት በጽኑ እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው ፈንጅ የማጥመድ ጥቃትም ሆነ የአርሲው እኩይ ተግባር ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምጽ የሰጠበትን ታሪካዊ የምርጫ ድል ለመቀማት የተወጠኑ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ድርጊቱን መነሻ በማድረግ እውነታን ለማዛባትና ሀገራዊ ግጭት ለመቀስቀስ የሚደረገውን የሚዲያና የሥነ-ልቦና ጦርነት በፅኑ የሚወገዝ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
በኦሮሚያ ክልል ታሪካዊና በቅድስና ስፍራቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ጨምሮ ከስድስት ሺህ በላይ አድባራትና ገዳማት ያሉ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ሕዝቡና የክልሉ መንግሥት ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ሌት ተቀን እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ ጥቃቱን የሃይማኖት አስመስሎ ማቅረብ ተጠያቂነትን የሚያስከትል አደገኛ አካሄድ መሆኑን አሳስበዋል።
በማህበራዊ ሚድያ ላይ ቤተክርስቲያን ስደት ላይ ነች በሚል ሀሰተኛ መረጃዎችን በማስተላለፍ ላይ እና የተለያዩ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባልም ተብሏል።
የእምነት ተቋማት የፖለቲካ ማስፈጸሚያ መሆን እንደሌለባቸው ያሳሰቡት የሰላም ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የበላይ አመራሮች ጋር ሰፊና ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን በመግለፅ በውይይቱ ስለ ጉዳዩ ምንነት፣ ስለ ጉዳቱ መጠንና ስለ አድራጊዎቹ ፍላጎት ሙሉ መግባባት ላይ መደረሱ ደርሰናል ብለዋል ።
በቀጣይም የሃይማኖት አባቶች በአካል ቦታው ድረስ ሄደው ሁኔታውን እንደሚመለከቱና መሰል ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ በጋራ የሚሰሩ ጉዳዮች ተለይተው እንደሚከናወኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ ሕዝቡም የጥፋት ኃይሎችን የሚዲያ ማወናበድ በመመከት የአብሮነት እሴቶቹን መጠበቅ አለበት በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ማለዳ
