ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሟን ለማጠናከር የሚያስችል የ70 ሚሊየን ዩሮ የረጅም ጊዜ ቀላል የብድር ስምምነት ከጣሊያን መንግስት ጋር ተፈራረመች።
ስምምነቱ የተፈረመው በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ አማካኝነት ነው። ይህ የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ታሰላ ከምትጠብቀው የ150 ሚሊየን ዩሮ አጠቃላይ የበጀት ድጋፍ ማዕቀፍ አካል መሆኑ ተገልጿል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ስኬታማ ውጤት አስመዝግባለች ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ ይህ ብድርም ሀገሪቱ የጀመረችውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትልቅ አጋዥ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለቀጣዩ የሪፎርም ምዕራፍ ትግበራ ከዓለም ባንክ ጋርም የአንድ ቢሊየን 450 ሚሊየን ዶላር ስምምነት መፈራረሟን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ በበኩላቸው፣ ጣሊያን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም ሂደት እንደ አጋር አገር በመደገፍ ሂደት ውስጥ ትቀጥላለች ብለዋል።
