ግዮን መጽሔት :- የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር (EREDA) እና ዶክሳ ቢዝነስ ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግ.ማ. ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በዶክሳ ቢሮ ዉስጥ የሁለቱ ተቋማት የስራ ሃላፊዎችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ነዉ ። የሀገሪቱን የሪል እስቴት ዘርፍ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማጠናከር፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስፋፋትና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ የመግባቢያ ሰነዶችን በዛሬው ዕለት በይፋ ተፈራረሙ።
ይህ ታሪካዊ ስምምነት በዘርፉ መሪ ሚና የሚጫወተውን የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር (EREDA) ተቋማዊ አቅም ከዶክሳ ቢዝነስ ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግ.ማ. የንግድ ልማት፣ የኢቨንት ዝግጅት፣ የባለድርሻ አካላት ትስስር እና እንደ ‘Kabod Expo 2025’ ያሉ ታዋቂ ፕሮግራሞችን በስኬት በማካሄድ የካበተ ልምድ ጋር ያጣመረ ነው።
ተቋማቱ ቀደም ሲል በጋራ ያከናወኗቸውን ስኬታማ ስራዎች ማለትም Addis Africa Real Estate Expo 2026፣ AFRES East African Regional Conference 2026 እና የ EREDA ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ 2026 መነሻ በማድረግ ወደፊትም ኤክስፖዎችን፣ ኮንፈረንሶችን፣ የኢንቨስትመንት ፎረሞችን እና የቢዝነስ ትስስር መድረኮችን በጋራ ለማዘጋጀት ዘላቂ ማዕቀፍ ፈጥረዋል።
- የሀገር ውስጥ ዘርፍን ማጠናከር፦
- የEREDAን ተቋማዊ ገፅታ ማጎልበት እና የአባልነት መስፋፋትን መደገፍ።
- የሪል እስቴት ዘርፍ ሙያዊ መመዘኛዎችንና ደረጃዎችን ማሻሻል፤
- በመንግስትና በግል ዘርፍ መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር።
- ዶክሳ ቢዝነስ ትሬዲንግ ለተመረጡ ፕሮጀክቶች የEREDA ተመራጭ የኢቨንት አስተባባሪ አጋር ሆኖ መስራት።
- ዓለም አቀፍ ትስስር እና የዲያስፖራ ተሳትፎ፦
-
- በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን (ዲያስፖራ) ያማከለ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንትና የትስስር መድረኮችን ማዘጋጀት።
- የውጭ ምንዛሬ ገቢን ማሳደግ፣ የባለሀብቶችን እምነት ማጠናከር እና ኢትዮጵያን በአፍሪካ የሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ማዕከል ማድረግ።
የመጀመርያዎቹ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች
በተደረሰው ስምምነት መሠረት የመጀመሪያዎቹ የኢንቨስትመንት ፕሮግራሞች በሚከተሉት ሀገራት በይፋ ይካሄዳሉ፦
- ሪያድ (ሳውዲ አረቢያ)፦ በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በቀጥታ የሚያገናኝ ትልቅ የኢንቨስትመንት መድረክ ማዘጋጀት።
- ጆሃንስበርግ (ደቡብ አፍሪካ)፦ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ሪል እስቴትና ኢንቨስትመንት ፎረም የአፍሪካ ገበያንና የአህጉሪቱን የንግድ ትስስር ማጠናከር።
- እስራኤል፦ በእስራኤል የሚኖሩ ዲያስፖራዎችን ከሀገራቸው የልማት እንቅስቃሴ ጋር የሚያስተሳስር ፕሮግራም ማካሄድ።
”ሕንፃዎችን መገንባት ብቻ አይደለም…”
የስምምነቱ አዘጋጆች እንደገለጹት ከሆነ፦
“የሪል እስቴት ዘርፍ ስራ ሕንፃዎችን መገንባት ብቻ አይደለም፤ የኢኮኖሚ እድገትን በእጅጉ ያግዛል፣ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል፣ የውጭ ምንዛሬን ያሳድጋል፣ እንዲሁም የአገራችንን ተወዳዳሪነት ያጠናክራል። እኛ ኢትዮጵያን ለዓለም እናስተዋውቃለን፤ ዓለምንም ወደ ኢትዮጵያ እናመጣለን!”
ሁለቱም ተቋማት በስምምነቱ ስር የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች በሙሉ ዝርዝር የፕሮጀክት ውሎችን በመፈራረም እንደሚተገበሩ ገልጸዋል። እነዚህ ውሎች የሁለቱን ወገኖች ኃላፊነት፣ የፋይናንስ አወቃቀር፣ የሥራ ጊዜ ሰሌዳ እና የአፈጻጸም መለኪያዎችን በግልጽ የሚወስኑ በመሆናቸው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዘላቂ አጋርነት ለመገንባት የሚያስችሉ ናቸው።
በመጨረሻም የመንግስት ተቋማት፣ የግል ዘርፉ፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ዲያስፖራው እና የልማት አጋሮች በሙሉ ይህንን ሀገራዊ ራዕይ በመደገፍ አብረው እንዲጓዙ ጥሪ ቀርቧል።
