በኢትዮጵያ 43 ሺህ የውጭ ንግድ ፍቃድ ያላቸው ነጋዴዎች ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ መሠረታዊ የሆነ የቴክኖሎጂ ኮሙኒኬሽን ሲስተም የሌላቸው በመሆኑ የዓለም አቀፍ ገዢዎችን እምነት ለማግኘት መቸገራቸው ተነገረ።
በአሎሃ ቪስታ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በተካሄደ የቢዝነስ ጉባኤ መድረክ ላይ እንደተጠቆመው፤ የሀገር ውስጥ የንግድ ተቋማት “በግለሰብ ስልክና ጥረት” ብቻ
ከመመራት ወጥተው ዘመናዊ አደረጃጀት ካልገነቡ የኤክስፖርት ዘርፉ ስኬታማ ሊሆን አይችልም።
የስትራቴጂ እና የቢዝነስ አማካሪው አቶ ሰለሞን ሲሳይ በመድረኩ ላይ፤ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ንግዳቸውን ተቋማዊ የማድረግ እና የረጅም ጊዜ ራዕይ ሰንቆ የመንቀሳቀስ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
እንደ አማካሪው ገለጻ፣ 43 ሺህ የኢምፖርትና ኤክስፖርት ነጋዴዎች ባሉባት ሀገር አብዛኞቹ ድርጅቶች የራሳቸው ዌብሳይትና የድርጅት ኢሜይል የሌላቸው መሆኑ፣ ከዓለም አቀፍ ገዢዎች ጋር ዘላቂ የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።
ይህ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ድክመት በኢትዮጵያ ላኪዎችና በውጭ ሀገር ገዢዎች መካከል “የእምነት ቀውስ” እንዲፈጠር ማድረጉም ተገልጿል።
አቶ ሰለሞን አክለውም፣ የሀገር ውስጥ አምራቾች እንደ ቡና እና ሌዘር ያሉ ምርቶችን በጥሬነታቸው ብቻ ለመላክ ከመቸኮል ይልቅ፣እሴት በመጨመር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆን “ብራንድ” መገንባት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ንግዶች ከግለሰብ ባለቤትነት ወጥተው ጠንካራ የሰው ሀብትና ግልጽ አደረጃጀት በመፍጠር ለትውልድ የሚሻገር ተቋም እንዲገነቡም ጥሪ ቀርቧል።
የሀገር ውስጥ ቢዝነሶች የጋራ አጋርነትን (Partnership Mindset) ካላዳበሩና ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ካላዘመኑ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይችሉ በዚሁ የአሎሃ ቪስታ የቢዝነስ መድረክ ላይ አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
