የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ የተዘጋጀው በሽርካ፣ መርቲ፣ ጀጁ፣ አርሲ ሲሬ፣ ሮቤ፣ ሙኒሳ፣ ጉና፣ ሆንቆሎ ዋቤ እና አሰኮ ወረዳዎች በተካሄደ የመስክ ምርመራ መሰረት መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።
ኢሰመጉ እንደሚለው፣ በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦች ለረጅም ጊዜ በሰላም ሲኖሩ ቢቆዩም፣ ባለፉት ዓመታት በታጠቁ ቡድኖች የተፈጸሙ ጥቃቶች በንጹሃን ላይ ያነጣጠሩ ሲሆን ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ እገታ፣ አስገድዶ መሰወር፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት እንዳስከተሉ ጠቁሟል።
በተጨማሪም መንግሥት ዜጎችን የመጠበቅ ኃላፊነቱን በሚገባ አለመወጣቱ ጥቃቶቹ በተደጋጋሚ እንዲቀጥሉ ምክንያት ሆኗል ሲል ገልጿል።
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በምስራቅ አርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በታጠቁ ኃይሎች በተለይም በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።
በእነዚህ ጥቃቶች በሽርካ 116፣ በመርቲ 117፣ በጀጁ 101፣ በሮቤ 47፣ በጉና 26፣ በሆንቆሎ ዋቤ 20፣ በሙኒሳ 19፣ በአሰኮ 5 እና በአርሲ ሲሬ 3 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመጉ መመዝገቡን ገልጿል። በተጨማሪም 4 የመንግሥት ሚሊሻ አባላት መሞታቸውንም ጠቅሷል።
በጉና ወረዳ ብቻ 26 ሰዎች መገደላቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፣ በናኖ ጃዊ ቀበሌ በአንድ ቀን 16 ሰዎች መገደላቸውን እና ከእነርሱ 5 ሰዎች በአንድ ጉድጓድ መቀበራቸውን ከቤተ ክህነት በተገኘ መረጃ ማረጋገጡን ገልጿል።
ኢሰመጉ በምርመራው ወቅት የተጎጂዎችን፣ የሟቾች ቤተሰቦችን፣ የዓይን እማኞችን፣ የቤተ ክህነት ኃላፊዎችን በማነጋገርና የመስክ ምልከታ በማድረግ ማስረጃዎችን እንዳሰባሰበ ገልጿል።
ኢሰመጉ ከኦሮሚያ ፖሊስ፣ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ እና ከሌሎች ተቋማት ምላሽ ለማግኘት ደብዳቤ ቢልክም፣ ሪፖርቱ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አልተገኘም ብሏል።
በመጨረሻም ኢሰመጉ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት እንዲያረጋግጡ፣ የጥቃት ፈጻሚዎችን ለፍትሕ እንዲያቀርቡ፣ ተጎጂዎች ካሳና ፍትሕ እንዲያገኙ እንዲሁም ተፈናቃዮች በደህንነት ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ አሳስቧል።
