ታላቋ የሀገር ባለውለታ ወ/ሮ መዓዛ ቅጣው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

Date:

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅነትና በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ከ40 ዓመታት በላይ በኃላፊነት ሲሠሩ የነበሩት ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው አረፉ።

ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው በ83 ዓመታቸው ያረፉት ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በአጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም ነው።

​ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው ሴቶች ከዩኒቨርሲቲ ለመመረቅና በከፍተኛ ኃላፊነት ተመድበው ለመሥራት ብርቅ በነበረበት ጊዜ በውጤት ያለፉ፣ በፋና ወጊነት በሚቆጠር አርአያነት፣ በከፍተኛ ተሳትፎ ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

​በ1950ዎቹ መጨረሻ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ ከዋሺንግተን ዲሲ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለወጣት ሴቶች ምሳሌ ለመሆን የበቁ ነበሩ።

​ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው ከ40 ዓመታት በላይ በኃላፊነትና በሥራ መሪነት ባገለገሉባቸው የግልና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አዳዲስ የሥራ ዘዴዎችን በመቀየስና የተቀናጀ አሠራር በማስለመድ ስማቸው በመልካም ሲጠራ ቆይቷል።

​በተለይም ለ19 ዓመታት በዋና ሥራ አስኪያጅነት የመሩትን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ትርፋማ ለማድረግ፣ አሠራሩን ለማዘመንና ጠንካራ ተቋም እንዲሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ በጊዜው በነበሩትና ሰነድ በሚመረምሩት ዘንድ የታወቀ ነው።

እንደ ፈጣን ሎተሪ ዓይነቶቹ ከጊዜው ጋር የተጣጣሙ አሠራሮች በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እንዲለመዱና የተጠናከሩ እንዲሆኑ ያደረጉት ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው ናቸው።

​በኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ በኅብረት ኢንሹራንስ፣ በናይል ኢንሹራንስ፣ በብርሃን ኢንሹራንስ በመመሪያ ሥራ አስኪያጅነት እየተመደቡ ተቋሞቹ እንዲጠናከሩ ሙሉ ልምዳቸውንና ችሎታቸውን ማስተላለፋቸውን አብረዋቸው የሠሩት እየመሰከሩላቸው ነው።

​ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው ትኩረትና ጥንቃቄ ከሚጠይቀው የሥራ መደባቸው ጋር ደርበው እንደ ቤተሰብ መመሪያ ማኅበር ከአንዴም ሁለቴ፣ እንደ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ እንደ ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅትና በመሣሰሉት ተቋማት ለረጅም ዓመታት በቦርድ ሊቀ መንበርነትና አባልነት፣ በሥራ አስፈጻሚነትም ጭምር ሲሠሩ ቆይተዋል።

​ዘለግ ላለውና ውጤታማ ለሆነ ሥራቸው የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል።

እስከ ሕልፈታቸው ድረስ ከሥራ ሳይለዩ በጥናትና በምርምር ሥር ቆይተዋል።

​የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው የቀብር ሥነ ሥርዓት ኮተቤ በሚገኘው በመካነ ቅዱሳን ሐና ወኢያቄም ቤተ ክርስቲያን ሐሙስ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ከቀኑ በ6:00 ሰዓት እንደሚፈጸም ቤተሰቦቻቸው ነግረውናል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በዓለም የምግብ ምርምር ድርጅት ሹመት ተሰጣቸው

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአግራ (AGRA) የቦርድ ሰብሳቢ...

አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በካናዳ ሀገር ሊሸለሙ ነው

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ መስራችና ሊቀመንበር አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በንግዱ...

በምክክሩ ወቅት በሀሳብ ልዩነት “አድማ የመቱ” ነበሩ

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ22ኛው ቀን ውሎው በስልታዊ ቡድን ደረጃ...

በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ያለዉ ግጭት እንዳሳሰበው የአውሮፓ ሰላም ፋውንዴሽን ገለፀ

የአውሮፓ ሰላም ፋውንዴሽን  በኢትዮጵያ ፌደራላዊ  መንግሥት እና በህዝባዊ ወያኔ...