ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የባህር ኃይል በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ፈንጂዎች ማስወገዱን ወይንም እንዲፈነዱ ማድረጉን አስታወቁ።
“ኢራን አዲስ ፈንጂዎችን የሚያስቀምጥ ማንኛውም መርከብ ወይም ጀልባ ወዲያውኑ እና በስልት እንደሚወድም ተነግሯታል” ሲሉ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ከኢራን እስካሁን ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም።
የባህር ወሽመጡ መዘጋት በዓለም ገበያዎች ላይ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲወዥቅ ምክንያት ሆኗል።
ትራምፕ አሜሪካ አካባቢውን እንደምትቆጣጠር በተደጋጋሚ ቢናገሩም ኢራን ግን ያለፈቃዷ ለመሻገር ሞክረዋል ባለቻቸው መርከቦች ላይ ተኩሳለች።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል ያልፍ ነበር።
አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ጦርነቱን የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ከጀመሩ በኋላ ግን ይህ ወሽመጥ ለመርከቦች እንቅስቃሴ ዝግ ሆኗል።
ኢራን የባህር ወሽመጥን ከመዝጋት በተጨማሪ በእስራኤል እና በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እንዲሁም በባህረ ሰላጤው ውስጥ ባሉ የአሜሪካ አጋሮች ላይ የበቀል እርምጃ ወስዳለች።
ጦርነቱን ለማስቆም ውይይቶችን ለማመቻቸት የተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት በመፍረሱ በአሜሪካ እና በኢራን መካከልም አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል።
ይሁን እንጂ በዚህ ሳምንት አሜሪካ በኢራን ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት ከኢራን ጋር በገንዘብ የሚተባበር ማንኛውም አገር እንደሚነጠል አስጠንቅቀዋል።
ኢራን እና አሜሪካ ሰኔ ወር ላይ ባለ 14 ነጥብ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ከኢራን ጋር በኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ጉዳይ ንግግር ከመጀመሩ በፊት በ60 ቀናት ውስጥ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ የጊዜ ገደብ ያስቀምጣል።
ኢራን በተደጋጋሚ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ለመታጠቅ ፍላጎት እንዳላት ለሚቀርብባት ክስ ፕሮግራሟ ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ የሚውል መሆኑን በመግለጽ ታስተባብላለች።
ይሁን እንጂ የጊዜ ገደቡ በማብቃቱ እና የታቀዱ ንግግሮች በመፍረሳቸው ትራምፕ የኢራንን አገዛዝ ይገረስሳል ሲሉ የጠሩትን ማዕቀብ ጥለዋል።
ኢራን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1979 እስላማዊ ሪፐብሊክ ከመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ አብዛኛውን ጊዜ ማዕቀብ ተጥሎባት ነው ያሳለፈችው።
የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ አሊ ማዳኒዛዴህ ቴህራን ሰፋፊ ማዕቀቦችን ለመቀበል “ሙሉ በሙሉ ዝግጁ” መሆኗን ተናግረው፣ ይህም ለአሜሪካ “ሌላ ሽንፈት” እንደሚያስከትል አክለዋል።
ይሁን እንጂ ኢራን በጦርነቱ ምክንያት እንዲሁም አሜሪካ ለሳምንታት ወደቦቿን በመዝጋት ምጣኔ ሃብቷ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጎዳ አድርጋለች።
ማክሰኞ ዕለት፣ ትልቁ የኢራን ነዳጅ ገዢ የሆነችው ቻይና የአሜሪካን “ሕገ ወጥ የአንድ ወገን ማዕቀብ” በጥብቅ እንደምትቃወም እና መብቷን ለማስጠበቅ “አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ” እንደምትወስድ ተናግራለች።
የአሜሪካው ባለሥልጣን የአሜሪካንን ማስጠንቀቂያ በመጣስ ከኢራን ጋር የንግድ እና የገንዘብ ልውውጥ የሚያደርጉ ወገኖች ከዶላር ግብይት ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ መነጠል እንደሚገጥማቸው አስጠንቅቀዋል።
