የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ባለፈው አመት 2016 ሐምሌ ወር ላይ የውጭ ምንዛሬ ግብይት በነፃ ገበያ እንዲመራ ከወሰነ በኋላ፣ አብሮ ይፋ በተደረገው መመሪያ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ አንዳንድ ማሻሻዎችን ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በመመሪያው ላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት መሰረት በማድረግም፣ ከህብረተሰቡ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ምንዛሪ መገበያየት ይቻላል ወይ ? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡
ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ይህን በሚመለከት የባንክ ባለሙያዎች ማብራሪያ ጠይቋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ዙርያ ማብራሪያቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡት የብሔራዊ ባንክ ባለሙያ ምን አሉ ?
” ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈቀደላቸው ሰዎች ውጪ፣ በውጭ ምንዛሪ መገበያየት አይፈቀድም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በውጭ ምንዛሪ ወይም ዶላር መገበያየት አይችልም፡፡
ግብይትን በዶላር የሚፈፅሙ ሰዎች፣ የተፈቀደላቸው ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህም ዶላር ይዘው ከውጭ የሚመጡ ቱሪስቶች፣ ዲያስፖራዎች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከውጭ ሲመጡ እስከ 10 ሺህ ዶላር ይዘው እንዲገቡ ስለሚፈቀድላቸው፣ በጉምሩክ አስመዝግበው ባስገቡት ዶላር መገበያየት ይችላሉ፡፡ “
አገልግሎት ሰጭዎችስ በዶላር ማስከፈል ይችላሉ ?
” እነዚህ ሰዎች በዶላር መገበያየት የሚችሉት፣ አገልግሎታቸውን በውጭ ምንዛሪ እንዲሸጡ ከተፈቀደላቸው ተቋማት ብቻ ነው፡፡
ለምሳሌ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጭዎች፣ ማለትም ሆቴሎችና አስጎብኝዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለሰጡት አገልግሎተት በዶላር ክፍያ መቀበል እንዲችሉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ያላቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ፣ በዶላር ግብይት መፈፀም አይችልም፣ ከተፈቀደላቸው ተቋማትም ቢሆን፡፡
እኔ ኢትዮጵያዊ ሆኜ በዶላር እንዲያስከፍል ወደ ተፈቀደለት ሆቴል ሄጄ በዶላር መጠቀም አልችልም፡፡ ዲያስፖራ ከሆነንክ ግን፣ የሆነ ሆቴል ሔደህ ለተሰጠህ አገልግሎት በዶላር መክፈል ትችላለህ፡፡ ሆቴል ደግሞ ለሰጠው አገልግሎት በዶላር የማስከፈል ፈቃድ ያለው መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከፋዩም፣ አስከፋዩም (ተጠቃሚውና አገልግሎት ሰጪው) በዶላር ለመገበያየት የተፈቀደላቸው ወይም እውቅና የተሰጣቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከአንድ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ ዶላር ማስተላለፍ ይቻላል ?
” የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፍን (ትራንስፈርን) በተመለከተ፣ ከአንድ የዶላር ሒሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ሌላ የዶላር ሒሳብ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፍ አይቻልም፡፡ ለምን ዓላማ ነው የሚተላለፈው ? የሚለው ይታያል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዕቃ ገዝተህ በዶላር ልክፈል ብትል፣ አንተም በዶላር የመክፈል መብት የለህም፣ ሻጩም በዶላር ክፍያ የመቀበል ፈቃድ የለውም፣ ስለዚህ አይቻልም፡፡
ነገር ግን የዶላር አካውንት ኖሮህ፣ ከውጪ ሀገር እቃ ብትገዛ፣ ለእሱ በዶላር የመክፈል መብት አለህ፡፡ በቀጥታ ለእቃ ሻጩ ነው ዶላሩ የሚተለላለፈው፡፡ ውጭ ሀገር እቃ ወደገዛህበት መደብር ትራንስፈር ይደረጋል/ይተላለፋል፡፡ መረጃ አቅርበህ፣ ባንኩ ያንን መረጃ አይቶ አሳማኝ ሆኖ ካገኘው ይህንን ያደርግልሀል፡፡ ከራስህ ዶላር መፅሐፉን ለሸጠልህ ነጋዴ በቀጥታ ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ ዋናው ነገር ለምን አላማ ነው የምታስተላልፈው የሚለው ነው፡፡ “
ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ግብይት መቼ ሊጀመር ይችላል ?
” በውጭ ምንዛሪ ግብይት መቼም አይጀመርም፡፡ በየትም ሀገር በውጭ ምንዛሪ ግብይት አይደረግም፡፡ እንደዛ ከሆነ፣ የሚነግርህ ትርጉም የሀገርህን ብር አታምነውም ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚዋ ችግር ላይ የወደቀባት ዚምባብዌ እንኳን ያንን አላደረገችም፡፡
የውጭ ምንዛሪ ፍሰትን ለመጨመር፣ ኤክስፖርትን ለማበረታታት፣ የምታደርጋቸው ማስተካከያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዛ ውጪ፣ ዜጎችህን በዶላር ተገበያዩ ልትል አትችልም፡፡
ለምሳሌ፣ ሪልስቴቶች ወይም አለምአቀፍ ት/ቤቶች የዋጋ እና የክፍያ ተመንን በዶላር ሲያወጡ ይታያል፡፡ ይህ ችግር የለውም፡፡ ክፍያው ሲፈፀም ግን በኢትዮጵያ ብር ነው የምትከፍለው፡፡ “
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በቀጣይ ፦
– ለውጭ ጉዞ ዶላር/የውጭ ምንዛሪ እንዴት ነው የሚሰጠው ?
– የባንኮች ቪዛ ካርዶች እንዴት ነው የምንጠቀምባቸው ?
– የባንኮች ቪዛ ካርዶች በሀገር ውስጥ የምንጠቀምበት ዕድል አለ ?
– የዶላር አካውንት/የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት ቅድመ ሁኔታ አለ ? በሚሉ ጥያቄዎች ላይ የባለሙያ ማብራሪያ ያቀርባል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
