የኢትዮስፕየ ነርሶች ማህበር ፥ የጤና ባለሙያዎች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ገለጸ። ጥያቄ ስለጠየቁ የታሰሩ ባለሙያዎች እንዲፈቱ እንዲሁም ዛቻና ማስፈራሪያዎች እንዲቆሙ ጠይቋል።
ማህበሩ ይህን ያለው በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች እየተካሄደ ባለዉ የጤና ባለሙያዎች ወቅታዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ በላከው መግለጫ ነው።
ማህበሩ ፤ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ለደረሰው የጤና ባለሙያዎች ጉዳይ መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል።
ማህበሩ ምን አለ ?
– በአሁኑ ሰዓት እየተነሱ ያሉት የባለሙዎቹ እና የማህበሩ አባላት ጥያቄዎች ማለትም፦
• የተቋማት ግብዓት እጥረት መኖር
• የደመወዝ ማነስ
• የጥቅማጥቅም አለመኖር
• የትምህርት እድል እና የደረጃ እድገት አለማግኘት
• የስራ ቦታ ደህንነት አለማግኘት … ለረዥም ጊዜያት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለውይይት ሲቀርቡ እና አጀንዳ ሆነው የቆዩ መሆናቸውን ገልጿል። ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑም ሁኔታው የመንግስትን ትኩረት እንዲያገኝ ጠይቋል።
– ” የህክምና አገልግሎት ተቋርጦ ወይንም ተስተጓጉሎ ጥያቄ ማቅረብ የጤና ተቋማቱም ሆነ ጤና ሙያተኛው ማዕከል የሆኑትን ታካሚዎች ለሞት ለእንግልት የሚዳርግ በመሆኑ የምንቀበለው አይደለም ” ያለው ማህበሩ ” ስራዎቹ በአስቸኳይ ወደነበሩበት እንዲመለሱ ሙያተኞቹ፣ የተቋማት ሃላፊዎችም ሆነ ጤና ሚኒስቴርና ባለድርሻ አካላት አፋጣኝ ውይይት እና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ” ሲል ጠይቋል።
– ” ጥያቄ ጠይቃችኋል ” ወይም ” አስተባብራችኋል ” በሚል ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ጤና ባለሙያዎች እንዲፈቱ ፤ በተቋማትም ሆነ በሌሎች አካላት የሚደረጉ ዛቻና ማስፈራሪያዎችም እንዲቀሙ ጠይቋል።
– ጥያቄ ያላቸው ነርሶችም ሆነ ሌሎች ሙያተኞች ለውይይት በሚዘጋጁ መድረኮች በመገኘት ጥያቄአቸውን እንዲያቀርቡ እና ለመፍትሄ ተባባሪ እንዲሆኑ ጠይቋል።
