ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ወደ ሠገር ውስጥ የገቡት ተሽከርካሪዎች ቁጥር 100 ሺህ እንደደረሰ የትራንስፓርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አሰፋ ሐዲስ፤ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከተያዘው እቅድ አንፃር ያነሰ አፈጻጸም እንዳላቸው ለአሐዱ ተናግረዋል።
ነገር ግን መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲገቡ የሕግ ማዕቀፎችን በማመቻቸቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመር እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በመጪዎቹ 10 ዓመታት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቿን ቁጥር 500 ሺሕ ለማድረስ አቅዳ እየሰራች ሲሆን፤ በዚህም መንግሥታዊ የሆኑ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በዘርፉ እንድሳተፉ ከፍተኛ ጥርት እየተደረገ መሆኑን አቶ አሰፋ ጠቁመዋል።
በዚህም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ብቻ ማብዛት ሳይሆን ጎን በጎን የቻርጅ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎችን ለማስፋፋት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የአገልግሎቱ ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፍ አክለዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ሲመጣ የኤሌክትሪክ ኃይል በቂ አቅርቦት እንድኖር ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለይ የቻርጅ አገልግሎት የሚሰጡ ጣቢያዎች ከመብራት መቆራረጥ ነፃ እንድሆኑ በስፋት ይሰራል ሲሉ አቶ አሰፋ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ብሎ ያስገባቸው 100 የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ባሶች እና ሚኒባሶች ከወራት በፊት የገቡ ሲሆን፤ በትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ስለመሆኑ የአገልግሎቱ ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ ጠቁመዋል።
