አብነት ሲራጅ
ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም እንደመግባት ከዛም ሲልቅ ከልቡ ተደስቶ ሲመለስ እንደማየት ምን የሚያስደስት ምንስ የሚያስመኝ ሌላ ደስታ አለ? በግጥር እንደ ሰውነት ካሰብነው ምንም መሆኑ የማይካድ ቃል ነው። ነገር ግን ሕዝብ ከመቅኖ ፍልፍሉ ሲታመም ሕመሙም ብሶበት በራሱ ሥፍራ መሄጃ መንቀሳቀሻ ታጥቶት እስትንፋስም ገዶት ኦክስጂን እንደሚጠቀም ህሙማን ሲጨነቅ እንደማየት የሚጨንቅ አንጀትስ የሚያቆስል ምን ነገር አለ?” እውነታው ምንም ነው ምክንያቱም አንዳችን ያለ ሌላችን ምንም ነን እና አንተ አንቺ ካልኖርሽ እኔ መኖር አልችልም። የኔ ሀገር ላንተ ሀገር ናት ያንተ ሀገርም ለኔ እንደዛናው ናት። ከዛም በላቀ ሁኔታ በደምህ ደሜን በደሜም ደምህ ተሰርቷል እና አንተ ሰላም ሲርብህ እኔም እንዳንተው ረሀብተኛ ስለሆንኩ ቡቡ ያ የፈገግታ ፊትህን እስካይ ይጨንቀኛል።
አንድነትህ ክፉውን የተንኮል ግንብ እንደ ጣት ላይ ቆሻሻ አሽቀንጥሮ ይጥላል። ሁላችንም አንድ ስንሆን በርካታ ነገሮችን የራሳችን ማድረግ ይቻለናል። በርግጥ ሁሉንም ሰው ቅዱስ አድርጎ መሳል ካለው የሰው ባህሪ አንፃር ከባድ የዕቁብ እዳ ነው። ከደቂቅ እስክ እልፍ ድረስ አንድ እንከን መኖሩ ርግጥ ነው ይሄንን ደግሞ ማስቆሞም ሆነ መግታት የሚቻለን በአንድነት እንደሚጠቀለል ሳር ተቋጥረን የጠነከረ ገመድ መሆን ሲቻለን ነው።
ሀገሬ ለኔ እና ለወገኔ ልትሆን የምትችለው ከሌባ እና አስመሳዮች ራሷን መታደግ ሲቻላት ነው። በርግጥ እንደ ሀገር አሁን ላይ ያለው የሕዝብ ተነሳሽነት ከሚባለው በላይ የኑሮ ዘይቤውን ከዲሞክራሲ ሥርዓት ጋር እያስኬደው ቢገኝም ካለው አጉራ ዘለል አካሄድ ጋር የሚደረጉ እሰጥ አገባዎች ሌላውን ዋጋ እያስከፈለው እንደመሆኑ መጠን ሕዝብ እና እኔ በጋራ ከድህነት ቀጥሎ ሌላ እድፍ የሆነብንን ሌብነት መከፈል ያለበትን ዋጋ ከፍለን ማስቆም አለብን።
በርግጥ የቱ ጋር ይጀምር ጥያቄ ቢሆንም ዋርካ አናቱ ላይ ካልሆነ ቅል አይበቅልበትምና እስካሁን በሕዝብ ሥም ተገብሮ በሌላው ሕዝብ ሥም የሚደረገውን ዘረፋ ተፀይፈን ልንቆምና የእለት ጉርሳችንን ሊያሳጣን የሚችለውን የሀገሪቷን የተበላሸ የአካሄድ ሥርዓት ከመቃወምም አልፈን ልናስቆመው ይገባል። ካልሆነ ግን ዘወትር በአጉል የጉንጭ ነጋዴዎች ላይ መሰል ነገር በሕዝብ ሕመም ሀገር ስትቆስል መኖር የለባትም የምንለው።
ሁሌም በራስ የበሽታ ድግስ ራስን የምንጎዳ ከሆነ የቁማር ቤት ጨዋታ ትርፋማ የሚያደርገው ባለቤቱን እንጂ ቁማርተኛውን እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባል። ይህ ሲባል ግን በፊንጢጣው የቆሰለ ቢኖር በወስፌ ብጣው እንዲሉት ከሆነ ነገሩ ሕመሙ ቁስለኛውን ቢያበረታበት እንጂ ለወኔ አንደበት ምኑም አይደለም።
ለሀገር መሥዕዋትነትንም ሆነ ነፃነትን ሊያመጣ የሚችለው ግለሰብ ወይም አንድ ተራ ነጋዴ አካል ሳይሆን ባለመብት የሆነው ራሱ ሕዝብ ነው። በገንዘብ የሚገዛም ሆነ የሚሸጥ የሸቀጥ ነፃነትም ሆነ ሰላም የለም። ሰላማችን ሁሌም አብሮን መኖር ያለበት እስትንፋስ ነው። ለዚህም አንዳችን ለሌላችን ጋሻ እና መከታ ሆነን መቀጠል ግድ ይለናል እና በጋራ ለምንኖርባት ሀገር አንድ ወጥ በሆነ አስተሳሰብ በጋራ መቆም አለብን።
አንዳችን ለሌላችን ስጋት እየሆንን በቀጠልን ቁጥር ቁስላችን በርትቶ የከፋውን ዘመን መጥራታችን አይቀርምና ሕዝባዊ ሕመምን መታገስ እንዲሉት የማይቻል ነውና ማስተዋልን የታደለ ትውልድ እንዳይሆን ነገር አድርጎ መሳሉ ዋጋ ያስከፍላል።
ለማንኛውም ሰው ከሀገሩ እና ከሕዝቡ ምንም የሚያስበልጠው ጥቅም ሊኖረው አይገባም እና ከሀገርህ የሚበልጥ ምንም የላቀ ሥራም ሆነ ሕይወት ሊኖርህ አይችልም። ልኑርም ብትል በሰቀቀን ራስህን እያሸማቀክ ከማኖር በዘለለ ቀን ውሎ ባደረ ቁጥር ካሰብከው ሳትደርስ የዱርዬ መዘባበቻ ሆነ ከመቅረት ባለፈ የሚኖርህ ጥቂት የሰውነት እስትንፋስ ይታጣኃል።
ከሰውነት የሚበልጥም ሆነ የሚያንስ ሰውነት የለም፡፡ በርግጥ አንተ ጠግበህ በልተህ በሞቀ ቤት ውስጥ ስለኖርክ እንዲሁም ለራስህ ቀምሰህ ገብተህ የምትወጣበት ቤት እና መከርሻ ስላለህ በመንገድ፣ በሥራ፣ እንዲሁም መኖርያ ቸግሯቸው በጎዳና ዳር የተሰጡትን እንደፌዝ አይተኸው ከሆነ አትጠራጠር፡፡ አንተም አንድ ቀን ተራው ይደርስህና ባለተራ እየተባባሉ ከመሳለቅ ባሸገር የምትከብርበትን ነፃነት ፈልጎ ማግኘት አሁን በእጅህ ብትሆንም ነገ ከሰማይ ርቃ በዳዴ ብትዳዳት መሳቂያ መሳለቂያ ከመሆን የሚያድንህ ወገን የህልም እንጀራ መሆኑ የማይቀር እዳ ነው።
ሁሌም መፍትሔዎችን በጦርነት መሻት ዘመኑ ያለፈበት ቢሆንም በዘመናችን እንዲህ ዓይነት ሂደቶችን ልንጠቀም የሚገባን ለመጨረሻ እና የሀገርን የሉዓላዊነት ለሚዳፈር አካል ሲሆን ለእርስ በእርስ ችግሮች ግን ልንጠቀመው የሚገባን መፍትሄ የሚሆነው ግን የሕንድን ሕዝብ ከእንግሊዝ ባርነት ያወጣውን የአስተሳሰብ እና ሕዝባዊ መሳሪያ መጠቀም ስለተቻላቸው ነው። በአመራሮች ደረጃም ቢሆን ለሕዝብ የሚሞቱ ጉምቱ ሰዎች ሲኖሩ መግቢያ ኖሯቸው የወለዱት ልጆች እንኳን በሕዝብ አንጀት ውስጥ ለዘላለም መኖር ይቻላቸዋል።
በዓለም ላይ ማትረፍ ያለብን ጥሩ ሥም እና ክብር ያለው ዝና እንጂ ጥለነው ልንሄድ እኛ ብልጥ ሌላውን ሞኝ አድርገን የምንስል ከሆነ ለምንወልዳቸው ልጆች ጭምር የመከራ ፅዋ ጥለንላቸው ማለፋችን የማይቀር ጣጣ ነው እና ብንችል እንደ ቶማስ ሳንካራ ሆነን ለሕዝብ ችግር ደርሶ በመፍትሄ ምርቃትን ብናገኝ ከምንም በላይ አዕምሯችን በባለፀግነት እርካታን አትርፎ ታሪካዊ ሰውም ለመሆን ይቻላል እና በሕዝብ ሕመም የማያመው ቢኖር መጨረሻውን ለራሱ ያስብበት። ሕዝብም የራሱን ልጅ ቀጥቶ የሚያስተካክለው ወላጁ ነው እና ካልሆነ ለጎልያድ የመቋጫ ዕድሜ ዳዊትን መጥራቱ አይከፋም። መልካሙን ሁሉ ለሕዝቤ!!
