በዐማራ ክልል የታወጀው ‹‹ሕግ ማስከበር›› ምን አስገኘ?

Date:

መንግሥት በአማራ ክልል ‹‹ሕግ አስከብራለሁ›› በማለት ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ግድያዎች እና ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ የሚከተሉት ሁነቶች ከሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የተፈጠሩ ናቸው፡፡

ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም የብልፅግና አመራሮች በፋኖ ጉዳይ መምከራቸው ተዘግቦ ነበር። በስብሰባቸውም የፋኖ እንቅስቃሴ በእጅጉ እንዳሰጋቸውና ፋኖ አንድ ጠንካራ መሪ ካገኘ መከላከያን ሊገዳደር የሚችል ኃይል ስለኾነ መሪ እንዳያገኝና ኃይሉንም የተለያዩ ስትራተጂዎችን በመንደፍና ድሮን ጭምር በመጠቀም ማዳከም እንደሚገባ ማንሳታቸው ተጠቁሟልል። ይህን መነሻ በማድረግም በማግሥቱ ሐምሌ 7 ቀን 2015 ዓ.ም የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽ/ቤት በሁሉም የአማራ ክልል ዞኖች ሚሊሻውን ለ7 ቀን አሰልጥኖ ፋኖን ለመውጋት የሚውል 53 ሚሊዮን ብር በጀት እንዲለቀቅለት ለአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮን በደብዳቤ ጠየቀ። በጀቱ ተፈቅዶላቸው ሥልጠናውን በሁሉም ዞኖች እንደሚጀምሩ ገልጸው ሥልጠናውን የማይሠለጥን ሚሊሻ መሣሪያውን ይቀማል የሚል አዋጅም አወጡ። ኾኖም ግን በቀጣይ ቀናት እንደታየው ሥልጠናውን ሊወስድ የሚችል ሚሊሻ በመጥፋቱና ይሠለጥኑ ዘንድ ተመልምለው የተላኩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚኒሻና የፖሊስ አባላት በመሠወራቸው ከ40 ሺህ በላይ ሠልጣኞችን ለማሳተፍ ያቀደው የክልሉ መንግሥት የሥልጠና ጊዜውን ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ ተገዷል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ምንውየለት ጭንቅሎ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ። በተመሳሳይ በዚያው ዕለት በሸዋሮቢት ከተማ የሚሊሻ አባል መኾኑ የተነገረለት አብዱልከሪም አባጀበል የሚባል ግለሰብ በጥይት ተገድሏል። በቀጣዩ ቀን ደግሞ ከሰዓት በኋላ በቆቦ ዙሪያ ባሉ ተራራማ አከባቢዎች በመድፍ እና ከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ መካሄድ ጀመረ፡፡ በዚህም የአካባቢው ፋኖዎች ባደረጉት የመከላከል ውጊያ የመከላከያ ሠራዊቱ ካምፕ ነው የተባለውን በመቆጣጠር የከፋ ውጊያ ሲካሄድ መሰንበቱን በርካታ የክልሉ ድምጽ የኾኑ ሚዲያዎች የፎቶና ቪዲዮ መረጃዎችን አካተው ዘግበውታል፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ሲደርስም መንግሥት ዝም ብሎ አልተቀመጠም ነበር፡፡ ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም በኮምቦልቻ ራስ መኮንን ሆቴል ውስጥ የተለያዩ የጦር መኮንኖች የተሳተፉበት ስብሰባ ተካሂዶ በ41 የተመረጡ የአማራ ክልል አካባቢዎች ልዩ ኦፕሬሽን እንዲደረግ ተወስኖ ነበር። 

በዚህም ከሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ መከላከያ በሰሜን እና በደቡብ ወሎ አካባቢዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጦርነት ከፈተ። በሰሜን ወሎ ላይ በግዳን ወረዳ፣ በደቡብ ወሎ ደግሞ በወግዲ፣ በቦረና እና በአማራ ሳይንት በርካታ ውጊያዎች ታካሂደው እንደታሰበው ፋኖ የተሰኘው ኃይል ላይ ድልን መጎናጸፍ አልተቻለም። በዚያው ሰሞን በጎንደር ማክሰኝት ከተማ ላይም ላይ አንድ የፋኖ አባል በክልሉ መንግሥት መታሠሩን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነገሰ፤ መንገዶችም ተዘጉ። ይሄን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት ከእንፍራንዝ ወደ ማክሰኝት ገባ። በግልባጩ የማክሰኝት ወረዳ አስተዳዳሪ ልጅ በአካባቢው ፋኖዎች ታገተ፡፡ በወቅቱ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ነጋ ብርሃኑ ከጥይት እንዳመለጡም ተጠቅሶ ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን የተነሳውን ውጥረት ለማርገብ ሲባል በሰጥቶ መቀበል መርህ ታፍኖ የነበረው የፋኖ አባልን በመልቀቅ የወረዳ አስተዳዳሪው ልጅ ከእገታው ነጻ ሊወጣ ችሏል፡፡ በማክሰኚት የነበረው ውጥረትም በጊዜያዊነት ሊረግብ ችሏል፡፡ ኾኖም ስምምነቱ መዝለቅ ሳይችል ቀርቶ ታፍኖ የነበረው የፋኖ አባል መሣሪያው ባለመመለሱ ምክንያት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በክልሉ የሚሊሻና የፖሊስ አባል ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ደርሷል፡፡

በሌላ በኩል ከሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሸዋሮቢት ከተማ ዳግም ያገረሸው የደፈጣ ጥቃት ድሽቃ እና ብሬን የታጠቁ ሁለት የመከላከያ ፓትሮሎች በፋኖ ጥይት ተደብድበው ተቃጥለዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋትም በርካታ የከተማዋና የአካባቢው የመንግሥት አመራሮች አካባቢውን ለቀው ወደአጎራባች ከተሞች ሸሽተዋል፡፡ አልፎም በወቅቱ እንደተዘገበው ሦስት ከፍተኛ የአካባቢው አመራሮች ለሕይወታችን ዋስትና የሚሰጠን ስለሌለ በሚል የሥልጣን መልቀቂያ አስገብተው ነበር። በተመሳሳይ ሐምሌ 11 ቀን  በደቡብ ወሎ ወግዲ ወረዳ ላይ በአብየ ጉርባ ቀበሌ በመከላከያ ሠራዊት 4 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከሟቾቹ መካከል የፀደይ ባንክ ሠራተኞች እንደሚገኙበት በወቅቱ ተጠቁሞ ነበር፡፡

በሌላ መልኩ የክልሉ ምክር ቤት ከሐምሌ 12 ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ቀናት መደበኛ ጉባኤውን አካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይም የአማራ ክልል ሕዝብ መሠረታዊ የኾኑ የማንነት ጥያቄዎች በሕግ የጸኑ እንዲኾኑ የተጠየቀ ሲኾን የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ራያ እና ጠለምት አካባቢ ሕዝብ ከህወሓት ግፍና ጭቆና ተላቆ መልሶ ያገኘውን ጥንተ አማራዊ ማንነት መንግሥት በሕግ አጽንቶ፣ በጀትም በጅቶ እንዲያለማ ማስቻል እንዳለበት የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በጉባዔው ላይ አንስተዋል። አልፎም በጉባዔው ላይ እንደአቶ ዮሐንስ ቧያለው ያሉ የምክር ቤት አባላት “እንዳለመታደል ኾኖ የአማራን ችግር እንዳንመክር፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ተከልክለን ተመልሰናል። ወይ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ጭራሽኑ ከአድዋ፣ ወይ ከበሻሻ በኾነ። ከእኛ ባልኾነ። የጊዜ ጉዳይ ካልኾነ ሁላችንንም ይገድሉናል። ለሥልጣናችን፣ ለሕልውናችን የተዋደቀውን ልዩ ኃይል አፈረሳችሁት። ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን፣ አማራን እናዋርዳለን ያሉት ጀነራሎች በነፃነት በሚንፈላሰሱባት ሀገር፣ እያነከሰ ያዋጋው ጀነራል ሕክምና ተከለከለ። ለአማራ የቆሙ አመራሮች ተገደሉ፣ ተባረሩ። ጠላቶቻችን በአንድነት ዘምተውብናል። ክልሉን ልክ እናስገባዋለን በማለት ተነስተዋል። መከላከያ ያለ ክልሉ ፍቃድ፣ አማራን እያተራመሰ ነው።” ወዘተ የሚሉ መረር ያሉ ሀሳቦች ተነስተዋል፡፡ በተጨማሪም ክልሉ የተነሳበትን በነፍጥ የታገዘ አብዮት ለመቀልበስ አምስት-አምስት አመራሮችን በመመልመል በ18ቱም ዞኖች ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ውይይት እንዲያደርጉ ስምሪት ሰጥቷል። እስከ ሐምሌ 26/2015 ዓ.ም ድረስ አጠናቀው እንዲጨርሱ መመሪያ ወርዶላቸዋል ተብሏል።

ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም መርሐቤቴ ከዓለም ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኘው ጎምሹ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ላይ በፋኖ አባላትና በመከላከያ መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በርካታ ጉዳት ደርሷል፡፡ መከላከያም ፋኖዎች ይኖሩበታል በሚል ጫካና ተራራውን በመድፍ ሲደበድብ ሰንብቷል። በርካታ ቁጥር ያለው የመከላከያ አባላትም ጉዳት እንደደረሰበት በወቅቱ ተመላክቶ ነበር፡፡ በተመሳሳይ በዚያው ዕለት በጎጃም በአዴት ከተማ የከተማው ፖሊስና ሚሊሻ በጥምረት በፋኖ አባላት ላይ ተኩስ ከፍተው ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ በማግስቱ ሐምሌ 14 ቀን ደግሞ በወልድያ ከተማ ድንገተኛ የተኩስ ልውውጥ ከአምስት በላይ ሰዎች ተገድለው በርካታ ውድመት ደርሷል፡፡ በተለይ አንድ የሁለት ልጆች እናት በቆሎሻጭ የነበረች ግለሰብ በተባራሪ ጥይት ተመትታ ወዲያውኑ ከልጆቿ ጋር ሕይወቷ ማለፉ አነጋጋሪ ኾኖ ሰንብቶ ነበር፡፡ ሐምሌ 15 ቀን ደግሞ በመካነሰላም ከተማ መከላከያ ሠራዊቱ በከፈተው ተኩስ ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች ሕይወታቸው ማለፉ እና በርካቶች መቁሰላቸው በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ሐምሌ 16 ቀን ደግሞ በጎጃም ጎንጂ ቆለላ ወረዳ፣ ሕዝብ እናወያያለን ብለው፣ ወደ ዋሸራ ቀበሌ ከዘለቁ የመንግሥት አመራሮች መካከል የአካባቢው የሚሊሻ ኃላፊ አውለው አላምር የተባለ ግለሰብ በፋኖ አባላቱ ሲማረክ የሰላም እና ደህንነት ኃላፊው ደግሞ ቆስሎ ወደ ባህርዳር ሆስፒታል መላኩን መረጃዎች ያመላክታሉ። በተመሳሳይ ሐምሌ 17 ቀን በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ አግሪት አካባቢ በፋኖ አባላቱና በአካባቢው ሚሊሻ መካከል በተካሄደ ውጊያ አምስት ሚኒሻ እና ሁለት ፖሊሶች ሲገደሉ ሁለት ፖሊሶች ተማርከዋል። በዚሁ ዕለት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ ቤት በቦንብ ተደብድቧል። በሌላ በኩል የክል፤ መንግሥት የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ ሐምሌ 18 ቀን ሁለት የፀጥታ ኃላፊዎችን ከስራ ማባረሩ ተሰምቷል። የተባረሩት ባለሥልጣናትም የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኮማንደር መንገሻ አውራሪስ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የፀጥታ አማካሪ ከፋለ እሱባለው መኾናቸው ተነግሯል። ሐምሌ 19 ቀን ደግሞ በጎንደር ምዕራብ ደንብያ ጯሂት ከተማ መከላከያ ከፋኖ ጋር ከፍተኛ ውጊያ ውስጥ መግባቱ ተጠቁሟል፡፡ ከተማውም ሙሉ ለሙሉ መውጫ መንገዶች ተዘግተዋል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ሴቶችን በቤት ውስጥ በማገዝ  መልካም ማህበረሰብ መፍጠር ተጀምሯል

በቤት ውስጥ የሚሠሩ ተግባራትን ተከፋፍሎ በመሥራት ሴቶችና እናቶችን መደገፍ...

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...