ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ተጠቃሚዎች መተግበሪያው የሚነግሯቸውን ሁሉ በጭፍን ማመን እንደሌለባቸው የጉግል ኩባንያ አካል የሆነው አልፋቤት ዳይሬክትር ሰንዳር ፒቻይ ተናገሩ።
ዳይሬክተሩ የ AI ሞዴሎች ለስህተት የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሰዎች ከሌሎች መተግበሪያዎችጋር በማጣመር እንዲጠቀሙባቸውም አሳስበዋል።
“ሰዎች የጉግል ፍለጋን እና ትክክለኛ መረጃን በመስጠት ላይ የበለጠ ተአማኒነት ያላቸው ሌሎች ምርቶችን የሚጠቀሙት ለዚህ ነው” ያሉት፡፡
ሆኖም አንዳንድ ባለሙያዎች ጉግልን የመሰሉ ትላልቅ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች የመሣሪያዎቻቸውን ውጤት እንዲያጣሩ ከመጋበዝ ይልቅ መተግበሪያቸውን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ ትኩረት መስጠት አለባቸው ይላሉ።
“ትክክለኛውን መረጃ ለመስጠት በምናደርገው ሥራ ኩራት ይሰማናል፣ ነገር ግን አሁን ያለው የተሻለ የAI ቴክኖሎጂ ለአንዳንድ ስህተቶች የተጋለጠ ነው” ብለዋል።
የጉግል መፈለጊያ መተግበሪያ የሆነው AI Overviews በአንዳንድ ያልተጠበቁ እና የተሳሳቱ ምላሾች ምክንያት ትችት ሲወርድበት እንደነበር ይታወሳል።
የለንደን ኩዊን ሜሪ ዩኒቨርሲቲ የAI ፕሮፌሰር የሆኑት ጂና ኔፍ፣ ስለጉዳዩ ሲናገሩ “እነዚህ ቻትቦቶች እውነተኛ ያልሆኑ መልሶችን እንደሚፈጥሩ እና ይህንንም የሚያደርጉት እኛን ለማስደሰት እንደሆነ እናውቃለን፤ ትልቁ ችግርም ይኸው ነው” ብለዋል።
“ስለ ጤንነት፣ ስለ አእምሮ ደኅንነት፣ ስለ ሳይንስ ወይም ስለ ዜናዎች የተሳሳተ መረጃ መስጠት ትልቅ ችግር የሚፈጥር ነው” ሲሉም አክለዋል።
ጉግል በAI ምርቶቹ እና በትክክለኛነታቸው ላይ ኃላፊነቱን ለተጠቃሚዎች ከማስተላለፍ ይልቅ የበለጠ ሃላፊነት እንዲወስድም አሳስበዋል።
ዘገባው የቢቢሲ ነው።
