አዳዲስ ብድር በመውሰድ ረገድ ጥንቃቄ እንድታደርግ ኢትዮጵያን ያስጠነቀቀው IMF ይህ የእዳ ተጋላጭነቷን ለመቀነስ አስፈላጊ ነው ሲል አሳስቧል፡፡
ተቋሙ አምስተኛውን የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ግምገማ ማጠናቀቁን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ተጨማሪ 464 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ ማፅደቁን ተናግሯል፡፡
ይህ ከሁለት አመት በፊት ያፀደቀውና ለአራት አመት በሂደት የሚለቀቅ በሚል የፈቀደው የ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አካል ነው፡፡
ከትናንት በስትያ IMF የስራ አመራር ቦርድ ያፀደቀው የ464 ሚሊዮን ዶላር ብድር እስካሁን በአራት ዙር ከተለቀቀው ሁሉ የላቀ ሲሆን ለወደፊቱ ከሚለቀቀው ብድር ታሳቢ የሚደረግ የ200 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ የታከለበት መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ለዚህም የኢራን ጦርነት የፈጠረባትን ጫና ለማቃለል እንዲያግዛት ታስቦ የተለቀቀው ገንዘብ ከከዚህ ቀደሞቹ የበለጠ እንዲሆን መደረጉንም መግለጫው ጠቅሷል፡፡
እስካሁን ድረስ ጠንካራ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ቢስተዋልም የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጫና መፍጠሩ በIMF መግለጫ ተጠቅሷል፡፡
በመሆኑም በተለይም የነዳጅ ዋጋ በአለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ እና ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ከውጭ በሚገባ ነዳጅ ላይ ጥገኛ በመሆኗ በአምስተኛው ዙር ግምገማ IMF ተጨማሪ የ200 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በመፍቀድ 464 ሚሊዮን ብድር እንዲፈቀድ ወስኗል፡፡
ይህም እስካሁን ከተቋሙ የወሰደችውን ብድር ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር አድርሶታል፡፡
በተጨማሪም ከIMF ጋር የተደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለቷን ለመሙላት ከብሔራዊ ባንክ ብድር መውሰድ ወይም የገንዘብ ማተም ማቆሟን መናገሯ ይታወሳል፡፡
በመሆኑም አሁን የተለቀቀው ከፍ ያለ ዶላር የሚፈጥረውን የበጀት ጉድለት ለመሙላትና የክፍያ ሚዛኗን እንድትጠብቅ የሚያስፈልጋትን ገንዘብ ለማሟላት ያግዛታል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በአምስተኛው ዙር የIMF ግምገማ ኢትዮጵያ የገቢ ግብር አሰባሰቧን በማሳደጓ ፣ የውጭ ምንዛሬ አሰራርንም በማሻሻሏ ተወድሳለች፡፡
ያለባትን የውጭ እዳ ለማሸጋሸግ ከአበዳሪዎቿ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶችን መፈራረሟ እና ከአለም አቀፍ የንግድ አበዳሪዎቿ ጋርም የምታደርገው ድርድር መሻሻል ማሳየቱን በበጎ እንደሚመለከተው IMF ተናግሯል፡፡
ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎቿ ጋር በመርህ ደረጃ ስምምት ላይ መድረሷንም IMF እንደተቀበለው በመግለጫው አካቷል፡፡
በሌላ በኩል ግን የስራ አስፈፃሚ ቦርዱ ተጨማሪ አዳዲስ ብድሮችን በመውሰድ ረገድ ጥንቃቄ እንዲደረግ መክሯል፡፡
