ህወሓት “የፌዴራል መንግሥት ላለፉት አሥር ወራት በትግራይ የነዳጅ አቅርቦት መገደቡ፣ በትራንስፖርት፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና መሠረታዊ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ መስተጓጎል ፈጥሯል” ሲል ገለፀ፤ ይህም የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር ላይ ሥጋት መፍጠሩን ጠቅሷል።
ህወሓት ትናንት ታኅሣሥ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያስተላልፈውን የበጀት ድጋፍ ማገዱን ገልጿል።
ይህም የጤና፣ የትምህርት፣ የውኃ እና የጽዳት አገልግሎቶችን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ ከማድረጉም በላይ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ሳይከፈላቸው እንዲቀሩ ማድረጉን አስታውቋል።
መግለጫው አክሎም በትግራይ መልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኤፈርት) ሥር ያሉ የኩባንያዎች የባንክ ሂሳብ መታገዱን ኮንኗል። ይህም የድርጅቶቹ የሥራ እንቅስቃሴ እንዲቆም እና በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያለ ደመወዝ እንዲቀሩ ማድረጉን ገልጿል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ የሚገባውን የነዳጅ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ ከገደበው አሥር ወራት ሊሞላው ተቃርቧል” ያለው ህወሓት “ይህም የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርትን፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም ለሴቶችና ለሕፃናት የሚሰጡ የድንገተኛ አምቡላንስ አገልግሎቶችን ጨምሮ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ሽባ አድርጓል” ሲል ገልጿል።
ፓርቲው የእነዚህ እርምጃዎች ድምር ውጤት በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የተጣለ “ዳግም ከበባ” ነው ሲል ገልጾታል። ይህም በሰላም ሂደቱ ላይ ያለውን እምነት ሊሸረሽርና ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም በኋላ የተገኙ ውጤቶችን ወደኋላ ሊመልስ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ህወሓት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርቧል። አክሎም ሁኔታው ይበልጥ እንዳይባባስና በክልሉ ያለውን ሰላም ለመጠበቅ ሲባል፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲያንሰራራ፣ የመንግሥት ዘርፉ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኝ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ ድጋፍ እንዲደረግ አሳስቧል።
ህወሓት ከዚህ በፊት ባወጣው መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥት በኤፈርት እና በሌሎች በትግራይ በሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ላይ የጣለውን ገደብ ኮንኖ ነበር። እነዚህ እርምጃዎች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የሚጥሱና የክልሉን የኢኮኖሚ ማገገም አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው ሲልም መግለጹ ይታወሳል።
መግለጫው ኤፈርት በትግራይ ክልል የሰዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ በመደገፍ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ከጦርነት በኋላ በማቋቋም ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው አጽንኦት ሰጥቷል። ድርጅቱ ወደ ሥራው እንዳይመለስ መከልከል፣ አሁንም በጦርነቱ መዘዝ እየተሰቃየ ላለው ሕዝብ የኢኮኖሚ ችግሩ እንዲራዘም ያደርጋል ሲልም አክሏል።
“እገዳው ሌሎች የትግራይ የፋይናንስ ተቋማትንም እንደሚነካ” የገለጸው ፓርቲው፤ ይህም “የካፒታል፣ የብድር እና የኢንቨስትመንት አቅርቦትን እንደሚገድብ” ጠቁሟል። “ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ማነቃቃት ወሳኝ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ እንዲህ ያሉ እርምጃዎች ድህነትን ሊያባብሱና የማገገም ሂደቱን ሊያስተጓጉሉ እንደሚችሉ ፓርቲው አሳስቧል”።አስ
