የኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያ ፣እገታ እና ዝርፊያ በሚመለከት ልዑካኑን በአካባቢው በመላክ በጉዳዩ ላይ ሲያደርግ የቆየውን ጥናት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
በቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ውጤት መሰረትም ገባኤው ጥቃቱ አንድን ሃይማኖት እና ብሄርን ትኩረት ያደረገ ግድያ ተፈጽሟል በማለት ሲዘዋወር የነበረውን መረጃ አጣጥሏል።
ጉባኤው ሪፖርቱን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ሲል የጠራው ” ያላለቀ በመሆኑ ፣የተጠቀሱት ወረዳዎች የተራራቁ በመሆናቸው እንዲሁም መሰረተ ልማት ውስንነት ያለበት ከመሆኑ አንጻር ሁሉም ቦታ ላይ ደርሶ የመጨረሻ ሪፖርት ለማውጣት ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ ነው ” ብሏል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ” ጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ በምስራቅ አርሲ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በተለይም በአምስት ወረዳዎች የተፈጠረ ክስተት አለ በእዚህም የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል ፣የተፈናቀሉ እና የጠፉ ንብረቶች ብዙዎች አሉ ” ሲሉ ክስተቱን በተመለከተ መብራሪያ ስጠተዋል።
ጉባኤው በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀው ጉዳዩን በአካባቢው በመሄድ አጣርተው የመጡት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የተወከሉ ሦስት ፣ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና ከኦሮሚያ እስልምና ከፍተኛ ምክር ቤት ሁለት፣ ከጉባኤው ሁለት ባለሞያዎች በአጠቃላይ በዋና ሰብሳቢ፣ በምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም በጸሃፊ የተዋቀረ 10 ልኡካን ናቸው።
ቀሲስ ታጋይ ” ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ምልከታ እና የማጣራት ሪፖርት ነው፣ ቀጣይ ተጨማሪ ማጣራት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ ቦታው ድረስ እየሄዱ የማጣራት ስራ ጊዜ የሚፈልግ ነው በሦስት እና በአራት ቀናት ብቻ የሚያልቅ አይደለም ወራትም ሊወስድ ይችላል” ነው ያሉት።
የአጣሪ ኮሚቴው ሰብሰቢ መላከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የመጀመሪያ ደረጃ የጥናት ሪፖርቱን ውጤት በሚመለከት ምን አሉ ?
” ዝርዝር ሃሳቡ በዋናው ማጠቃለያ ሪፖርት ላይ የሚገልጽ ሆኖ ጥናቱ የተደረገው ጉና፣ ሽርካ ፣ሆንኩሎ አቤ፣ መርቲ ወረዳዎች ናቸው።
አንደኛ በጉና ወረዳ ናኖ ጃዊ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የሰው ህይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም ፣ዝርፊያ እንዲሁም እገታ ተፈጽሟል።
የክስተቱ ሁኔታ 12/02/18 ዓም ከቀኑ ስምንት ሰአት ታጣቂዎች አስገድደው ከማህበረሰቡ ጋር ምሳ በሉ በመጨረሻም የመንግስት ታጣቂ ሃይል መምጣቱን ሲያውቁ የተወሰኑ ሰዎችን አግተው እና ንብረት ይዘው ወደ ጫካ ሸሹ።
13/02/18 ዓም ምሽት ተመልሰው ተጨማሪ ሰው አግተው ወሰዱ።
14/02/18 ዓም ያገቷቸውን ሰዎች ገደሏቸው ከተጎጂ ቤተሰቦች እና ካነጋገርናቸው ሰዎች በተሰጠ ምላሽ ይህንን ድርጊት የፈጸሙት ራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት/ሸኔ፣ ወይም ፋኖ ናቸው የሚል ምላሽ ነው።
አንዳንድ ግለሰቦች ደግሞ በሰጡት ምላሽ ማንነታቸውን እንደማያውቁ ነገር ግን በለሊት የሚንቀሳቀሱ ምንም አይነት የሃይማኖት መገለጫ የሌላቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ነው።
ሁለተኛ በሸርካ ወረዳ 17/02/18 ዓም የሰው ህይወት ጠፍቷል እገታም ተፈጽሟል በወረዳው የተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ ዜጎች ላይ በተለያየ ጊዜ ዘር ፣እምነት እንዲሁም እድሜ እና ጾታ ሳይለዩ ግድያዎች ተፈጽመዋል።
ህጻናት ታግተው ገንዘብ መጠየቂያ ተደርገዋል፣ ወላጆች ገንዘብ መስጠት ስላልቻሉ ህጻናቱ ተገድለዋል።
አንዳንድ ቦታዎች ላይ ህጻናቱ ተለቀው ወላጆች ከነገንዘባቸው ተወስደው ተሰቃይተዋል።
የተቀሩት ወረዳዎችም ተመሳሳይ ድርጊቶች መከናወናቸው ምላሽ ተሰጥቶናል።
የመንግስት በኩል የተገኘው ምላሽ ወታደራዊ እርምጃ መወሰዱን እና በመንግስት መዋቅር ጭምር መስዋዕትነት እየተከፈለ መሆኑን ተገልጾልናል።
በችግሩ ተጋላጮች ክስተቱ አንድ ወገንን ወይም ብሔር እና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ አለመሆኑን እና ሁሉንም የጎዳ መሆኑን ተገልጾልናል።
አጥኚ ቡድኑ በአራት ወረዳዎች በመንቀሳቀስ እና እውነታውን ለባለድርሻ አካላት ለማቅረብ ስራውን የጀመረ ሲሆን በአራት ወረዳዎች ባስቀመጠው የጥናት እቅድ መሰረት ተግባራዊ ስራውን ያከናወነ በመሆኑ ጥቅል ዝርዝር ሁኔታዎች ማለትም የሟች ማንነት ፣የአሟሟት ሁኔታ፣ ብዛት ፣የሃይማኖት ስብጥር በቀጣይ በጥናት የሚካተቱ እና የቀሩትን ወረዳዎች ባማከለ መልኩ የሚያቀርብ ይሆናል ” ብለዋል።
ምክትል ሰብሳቢ ሃጂ አብድልሃኪም ሁሴን በሰጡት ቃል አንድ ወገን ላይ ያተኮረ ግድያ ተፈጽሟል መባሉ ስህተት መሆኑን ገልጸው ” አጥቂዎቹ አንድን ሃይማኖት እንደማይለዩ ፣እንዲሁም ታጣቂዎቹ የሁሉም ሃይማኖት ስብጥር እንደሆኑ በአንዳንድ ወቅት በአጋቾቱ ታግተው ከተለቀቁ ሰዎች በተገኘ መረጃ ተገልጾልናል ” ብለዋል።
@tikvahethiopia
