ራሚስ ባንክ በሀገሪቱ ውስጥ የነበረውን የፋይናንስ ዘርፍ አካታችነትና የተሟላ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ የለውጡ መንግስት ባደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ ሰኔ 4 /2023 እ.ኤ.አ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የባንክ ስራ የመጀመር ፈቃድ በማግኘት በ6 ሺ 325 ባለአክሲዮኖች፣ በ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን የተመዘገበ ካፒታል ወደ ስራ የገባ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ ነው።
ራሚስ ባንክ በ2024/25 የበጀት አመት ከ 400 ሚሊየን ብር በላይ ጠቅላላ ገቢ (Net Operating Income) በማስመዝገብ ስኬታማ የእድገት ጉዞውን አስጀምሯል። ይህም ባለፈው በጀት አመት ካስመዘገበው ጠቅላላ ገቢ የ 3 ሺ 726 በመቶ እድገት ያሳየ ሲሆን የተጣራ ትርፉን በ 101 በመቶ ማሳደግ ችሏል።
ባንኩ ጠቅላላ ሀብቱን በማሳደግ በተጠቀሰው የበጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ አድርሷል፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በመቶኛ 85 በመቶ ጨማሪ አሳይቷል፡፡
እንዲሁም የደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ173 በመቶ ማሳደግ ችሏል። በተጨማሪም በንኩ 20 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያሰባሰበ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 7 ሺ 780 በመቶ ጨማሪ አሳይቷል። የደንበኞች ተደራሽነትን በሚመለከት 47 ቅርንጫፎችን ለአገልግሎት ክፍት ያደረገ ሲሆን አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት ረገድ ደግሞ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጠቅላላ ወደ 352 ሺ ደንበኞችን በማፍራት የደንበኞቹን ቁጥር በ 93 ቀመቶ አሳድጓል።
ከዲጂታል አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ራሚስ ባንክ ለደንበኞቹ ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የባንክ አገልግሎት አሰጣጡን እያዘመነ የሚገኝ ሲሆን። ይህንንም ተከትሎ የዩኤስ-ኤስዲ(USSD) ተጠቃሚ ደንበኞችን ቁጥርበ1 ሺ 802 በመቶ ከፍ እንዲል ከፍተኛ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ ማገባደጃ ላይ ደግሞ የራሚስ ሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያንና የካርድ ባንኪንግ አገልግሎቶቹን ለደንበኞቹ በማስተዋወቅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስቸሏል። ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት በመረዳት የላቁ የዲጅታል ባንክ አማራጮችን እንደ ኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ዋሌት እና ኢ-ሙራባሃ የዲጀታል አገልግሎቶችን ለመተግበር በፍጥነትና በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
ራሚስ ባንክ በ2024/25 የበጀት ዓመት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን ሲያከውን የቆየ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ኩነቶችን በመፍጠር በሰፊው ማህበረሰብ ልብ ዉስጥ እንዲኖር አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል። በቀጣይነትም ማህበረሰብ ተኮር ስራዎችን በሰፊው ለመስራት እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ባንኩ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ያለውን አጋርነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክርአድርጓል። ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ ራቢ ሼህ ሁሴን ፣ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዓሊ አህመድ፣ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከድር አባስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
