ሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተወሰነበትን ዉሳኔ በመቃወም ለዓለም አቀፉ ስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት July 11/ 2025 አቤቱታ ማስገባቱ ይታወቃል።
ክለቡ ለዓለም አቀፉ ስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ያስገባው ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ በኬዝ ቁጥር CAS 2025/A/11595/Sidama Bunna V. Ethiopian Football Federation CAS 17,July በሚል መመዝገቡን ለክለቡ ይፋዊ ኢ-ሜል አድራሻው ላይ በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።
የዓለም አቀፉ ስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ከJuly 11/2025 ጀምሮ እስከ July 16/2025 ድረስ ከክለቡ በይግባኙ ዙሪያ አስፈላጊ መረጃዎችንና ማብራሪያዎችን በኢሜል እየጠየቀና ከክለቡም እየተሰጠዉ ከቆየ በኋላ፣ አስፈላጊ መረጃዎች በሙሉ መቅረባቸዉን አረጋግጦ July 17/2025 ጉዳዩን ለመመልከት በይፋ መቀበሉን አረጋግጧል።
CAS ጉዳዩን መቀበሉን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ኢሜል መግለፁ የታወቀ ሲሆን፤ እንዲሁም ለዓለም የእግር ኳስ ማህበር FIFA እና ለአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፈደረሽን /CAF/ በግልባጭ አሳዉቋል።
በቀጣይም አሰራሩ በሚፈቅድ መልኩ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ቦርድ ለመላው የክለቡ ደጋፊዎች እና የስፖርት ቤተሰብ በሙሉ ጉዳዩ የደረሰበትን እየተከታተለ እንደሚያሳዉቅ እየገለፀ፤ የክለቡ ደጋፊዎች በሙሉ ነገሮችን በትዕግስት እየተከታተሉ እንዲቆዩ ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል።
(የሲዳማ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)
